በአንድ ጀምበር የ700 ሚሊየን ችግኝ ተከላ በመላው ሀገሪቱ አትዮጵያውያን ከማለዳ 12:00 ሰዓት ጀምሮ በነቂስ በመውጣት አሻራቸውን ማኖር ጀምረዋል።
ላለፍት 6 አመታት 40 ቢሊየን ችግኝ የተከለችው ኢትዮጵያ ዘንድሮም 7.5 ቢሊየን ለመትከል አቅዳ እየሰራች ነው።
ባለፋት አመታት ኢትዮጵያውያን በአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሀ ግብርም የነቃ ተሳትፎ በማድረግ የራሳቸውን ክብረወሰን በየአመቱ በማሻሻል ታሪክ ሰርተዋል።
የዘንድሮው የአንድ ጀንበር የ700 ሚሊየን ችግኝ ተከላ መጀመርን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ደኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ የመቻል አቅማችንን የምናሳይበት ነው ብለዋል።
ለአለም አካባቢ ጥበቃ ከፍተኛ አበርክቶን እየተወጣች ያለችው ኢትዮጵያ በዚኸኛው መርሀ ግብርም አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ለመጻፍ ተዘጋጅተናል ብለዋል።
የችግኝ ተከላ ቦታዎች ላይ የግብርና ባለሙያዎች እንደሚገኙ የተናገሩት ሚኒስትር ደኤታው እንዳለፉት አመታት ሁሉ የመትከያ ቦታዎች በጂኦ ሪፈረንስ ተደግፈው ወደ አንድ የመረጃ ማደራጃ ማዕከል የመረጃ ቋት ይላካሉ ብለዋል።
ኢትዮጵያውያንም በነቂስ በመውጣት ታሪካዊ ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ፍቃዱ መለሰ