በኦሮሚያ ክልል ሕዝቡ ችግኝ በመትከል ያሳየውን ተነሳሽነት በእንክብካቤም መድገም እንደሚገባው የክልሉ ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ አስገነዘቡ።
የዘንድሮው የአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር እየተካሄደ ሲሆን አቶ ሽመልስ አብዲሳም በጅማ አረንጓዴ ዐሻራቸውን አኑረዋል።
በዚሁ ጊዜ አቶ ሽመልስ አብዲሳ እንደገለጹት፤ ባለፉት ሰባት ዓመታት በተከታታይ እንደ ሀገር እና እንደክልል ደረጃ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ስኬታማ ስራዎች ተከናውነዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ የክልሉ ሕዝብ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ተክሏል።
በዛሬው እለትም በክልሉ የአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በርካታ ሕዝብ በተሳተፈበት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህም ከችግኝ ዝግጅት እስከ ጉድጓድ ቁፋሮ በቂ ዝግጅት መደረጉን አስታውሰዋል።
ባለፉት ዓመታት በተተከሉ ችግኞች ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች እየተገኙ ሲሆን፤ ከሁሉም በላይ አረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቩ ሕዝቡ ተፈጥሮን ወደ መንከባከብ ነባር ባህሉ መመለስ መቻሉን አስረድተዋል።
በተለይም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በግብርና ልማት አመርቂ ውጤቶች እያስገኘ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ ተግባር ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል።
የክልሉ ሕዝብ በችግኝ ተከላው ያሳየውን ተሳትፎ በችግኝ እንክብካቤውም በመድገም ችግኙ ለውጤት እንዲበቃ ጥረቱን ማጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በዚህም በየሁለት ሳምንቱ ችግኞችን ውኃ በማጠጣት፣ በመኮትኮትና ከንክኪ በመከለል ለውጤት ማብቃት እንደሚገባም አሳስበዋል።