የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የአካባቢ ጥበቃን ለማሻሻል እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንዲሁም የተሻለች ሀገር ለትውልድ ለማስተላለፍ ሚናው የጎላ መሆኑን የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት አለሚቱ ኡመድ ገልጸዋል፡፡
ፕሬዚዳንቷ፣ እንደ ሀገር በአንድ ጀንበር 700 ሚሊየን ችግኞችን የመትከል መርሐ ግብርን በክልሉ አስጀምረዋል፡፡
በመርሐ ግብሩም፣ በክልሉ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ስራዎች ፍሬያማ ውጤቶችን አግኝተናል ብለዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት የተከልናቸው የፍራፍሬ ዛፎች አሁን ላይ ምርት መስጠት ጀምረዋል ያሉት ፕሬዚዳንቷ፣ ይህም የምግብ ዋስትናን በማሳደግ እና የቤተሰብን ገቢ በመጨመር እንዲሁም የክልሉን የአረንጓዴ ሽፋን በመጨመር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል፡፡
ዛሬ በሚካሄደው ሀገር አቀፍ በአንድ ጀንበር የ700 ሚሊየኝ ችግኞችን የመትከል መርሃ ግብር ላይም፣ በክልሉ ከ1.55 ሚሊዮን በላይ ችግኞች እንደሚተከሉ ተናግረዋል፡፡
ፕሬዚዳንቷ አክለውም፣ የክልሉ ህዝብ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን የግብርናው አካል አድርጎ በመውሰድ የክልሉን የአፈር ለምነትና የውሃ ሀብት በአግባቡ መጠበቅ ይገባዋል ብለዋል፡፡
የክልሉ ህዝብም በዚህ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በንቃት እንዲሳተፍም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡