የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በክልሉ ለወጣቶችና ሴቶች ሰፊ የስራ እድል መፍጠር ማስቻሉን አቶ አዲሱ አረጋ ገለጹ

You are currently viewing የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በክልሉ ለወጣቶችና ሴቶች ሰፊ የስራ እድል መፍጠር ማስቻሉን አቶ አዲሱ አረጋ ገለጹ

AMN ሐምሌ 24/2017

በኦሮሚያ ክልል የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለወጣቶችና ሴቶች ሰፊ የስራ እድል መፍጠር ማስቻሉን በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የክልሉ ገጠር ክላስተር አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋ አስታወቁ።

አቶ አዲሱ ዛሬ በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከምስራቅ ሸዋ ዞን አመራሮችና ነዋሪዎች ጋር በአደአ ወረዳ በመገኘት አሻራቸውን አኑረዋል።

አቶ አዲሱ በወቅቱ እንዳሉት አረንጓዴ አሻራ ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ በርካታ ስኬቶች የተመዘገቡ ሲሆን ከተገኙ ውጤቶች መካከል የዝናብ እጥረትን በመከላከል ምርታማነትን ማሳደግ መቻሉን ጠቅሰዋል።

የክልሉን የደን መመናመን በማስቀረት የደን ሽፋኑን በማሳደግ የላቀ እምርታ ማስመዝገቡንም አስታውቀዋል።

የደረቁና ለመድረቅ የተቃረቡ ሀይቆችና ምንጮችን መታደጉን ጠቁመው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።

በመርሃ ግብሩ በመታገዝ በርካታ የሥራ ዕድል መፍጠር የተቻለ ሲሆን በተለይም ወጣቶችና ሴቶች ችግኝ በማፍላትና በመንከባከብ በስፋት ተጠቃሚ መሆን ችለዋል ነው ያሉት።

በመርሃ ግብሩ በመነቃቃት ዓመቱን ሙሉ የዛፍ ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞችን ለግለሰቦችና ድርጅቶች በመሸጥ ገቢያቸውን ማሳደግ ችለዋል ብለዋል።

የተተከሉ ችግኞች ሙሉ በሙሉ እንዲጸድቁ ተስማሚ ቦታ ላይ መትከልና ባለቤት እንዲኖራቸው በማድረግ ረገድ በየቀበሌው የትውልድ ጥላ ስያሜ ተሰጥቶት ጥበቃና እንክብካቤ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ለሰው ልጅ እንክብካቤ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ችግኞችንም መንከባከብ አስፈላጊ ስለሆነ በበጋ ወቅት የእንክብካቤው ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

አረንጓዴ አሻራ ሀገራችንን ከፍ ሲልም ዓለማችንን ለኑሮ ምቹ ለማድረግ የአካባቢ ጥበቃ ተግባራትን በማስፋት አመርቂ ውጤት ማስገኘቱንም አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያም የደን ሀብቷን ወደ ነበረበት በመመለስ የብዝሃ ሕይወት ሀብቷን ከጥፋት ለመታደግ የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ ጠቀሜታ ዘርፈ ብዙ በመሆኑ የክልሉ ህዝብ በነቂስ ወጥቶ እየተሳተፈ እንደሚገኝ አውስተዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review