የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፍተኛ አመራሮች፣ የምክር ቤቱ ጽ/ቤት አመራሮች እና የጽ/ቤቱ ሠራተኞች የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አከናውነዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የአገራችን ሁለንተናዊ ዕድገት ዘላቂ እንዲሆን የሚያስችል መሆኑን የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
በመርሐ-ግብሩ ላይ፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የአገራችን ዕድገት ከተፈጥሮ ጋር የታረቀ እንዲሆን ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛልም ብለዋል።
በአካባቢ ጥበቃ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ርብርብ አበረታች ውጤት በመመዝገብ ላይ እንደሚገኝ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በዓለማችን አሳሳቢ የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝም ተስፋዬ (ዶ/ር) ጠቅሰዋል።
በአንድ ጀንበር 7 መቶ ሚሊዮን ችግኝ የመትከል መርሐ ግብር ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አገራትና ለዓለም ልምድ የሚቀሰምበት ተግባር እያከናወነች እንደምትገኝ ጠቁመዋል።
የዚህ ታሪክ አካል የመሆን ዕድል ያገኙ ኢትዮጵያዊያን ችግኞችን በመትከልና የተተከሉትን በመንከባከብ የተሻለች አገርን ለትውልድ ለማስተላለፍ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አስተላልፈዋል።