ኢትዮጵያ በየዓመቱ እያከናወነች የምትገኘው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በአርዓያነት የሚጠቀስ መሆኑን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።
የዘንድሮው 7ኛ ዙር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር “በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ ሐሳብ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታልሞ በመላ ሀገሪቱ ተከላው እየተከናወነ ይገኛል።
በዛሬው የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር 700 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል ስራ ተጀምሯል፡፡
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ አረንጓዴ ዐሻራቸውን አኑረዋል፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፣ በሰባተኛው ዓመት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በአንድ ጀምበር 700 ሚሊዮን ችግኞች የመትከል ስራ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
የአረንጓዴ ዐሻራ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለው መሆኑን አንስተው የህዝቡም ግንዛቤ ማደጉን ተናግረዋል፡፡
መርሐ ግብሩ የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል፣ የሥራ ዕድል ከመፍጠር፣ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አንጻር እንዲሁም ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ አኳያ እንዲሁም በርካታ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ህዝቡም የአረንጓዴ ዐሻራን ጥቅም በመረዳት በነቂስ በመውጣት እየተከለ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የአረንጓዴ ዐሻራ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ያለውን አደጋ በመቋቋም ረገድ ትልቅ ሚና ያለው መሆኑን ጠቁመው ሁሉም ድርሻውን ሊወጣ ይገባልም ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በአርዓያነት የሚጠቀስ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡