”በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ ሃሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወነ ያለው የአንድ ጀምበር 700 ሚሊየን ችግኞችን የመትከል መርሐ-ግብር በትግራይ ክልል እየተከናወነ ይገኛል፡፡
በክልሉ በፃዕዳ እምባ ወረዳ በይፋ በተጀመረው መርሐ ግብር፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚደንትን በመወከል የክልሉ እርሻና ገጠር ልማት ቢሮ ኃላፊ እያሱ አብርሃ (ዶ/ር) መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም የተፈጥሮ ሃብትን ማዕከል ያደረገ እርሻ ለመፍጠር፣ የአረንጓዴ ልማት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
ለዘላቂ ልማት ተፈጥሮን መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፤ በዛሬው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብርም በክልሉ ችግኞች እየተተከሉ ነው ብለዋል፡፡
የቢሮ ኃላፊው አያይዘውም የተተከሉ ችግኞችን በዘላቂነት መንከባከብ ይገባል ብለዋል፡፡
የመርሐ ግብሩ የተሳተፉ ነዋሪዎች ችግኝ መትከል እርጥበትን ለመያዝ፣ ምርታማነትን ለማሳደግ እና የአየር መዛባትን ለመከላከል እንደሚያግዝ ገልጸው፤ የተተከሉ ችግኞች እንዲጸድቁ በቀጣይም መንከባከብ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።