ለሀገር እድገትና ብልጽግና እንዲሁም ማንሰራራት የዛሬ ትጋት ወሳኝ ነው ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር ኢ/ር) ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ በዳውሮ ዞን ታርጫ ዙሪያ ወረዳ ጎሪቃ በርሳ ቀበሌ የአረንጓዴ ዐሻራቸውን አኑረዋል።
በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክትም ለሀገራችን የወደፊት እጣ ፈንታ የአሁኑ የልማት ጥረትና ትጋት ወሳኝ ነው ብለዋል።
በክልሉ ባለፉት ዓመታት የተሰሩ ስራዎች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ጥሩ መሰረት ያኖሩ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይም በተጠናከረ መልኩ መትከል፣ መንከባከብና ለፍሬ ማብቃት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ሀላፊ ማስረሻ በላቸው በበኩላቸው ባለፉት 6 ዓመታት በርካታ ችግኞች መትከል መቻሉን አስታውሰው ዘንድሮም በተጠናከረ መልኩ መቀጠሉን ተናግረዋል።
በዛሬው የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በሁሉም አካባቢዎች ዜጎች እስከ ምሽት ድረስ ዐሻራቸውን እንዲያኖሩ ጥሪ አቅርበዋል።