የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ሠራዊት የሀገራችንን ሰላምና ደህንነት ከማስከበር ጎን ለጎን ኢትዮጵያ በምታካሄዳቸው በማንኛውም የልማት ስራዎች ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
በአንድ ጀምበር 700 ሚሊዮን ችግኞች የመትከል መርሃ ግብርን በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ሰንዳፋ በኬ ከተማ ተጀምሯል።
ምክትል ኮሚሽነር ጀነራሉ በመልዕክታቸው የዛሬው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢንሼቲቭ ለሰባተኛ ጊዜ የተካሄደና መላዉ የሀገራችን ህዝብ እየተሳተፈበት ያለ ፕሮግራም መሆኑን ጠቅሰዋል።
እንደሀገር በመትከል ማንሰራራት በሚል መሪ ቃል ችግኝ ተከላ ስናካሄድ ደን ምን ያክል የአየር ለውጥ መዛባትን እንደሚያስተካክል እና ሀገራችን ላይ ያሰብነውን አረንጓዴ ልማት ለማሳካት እየተደረገ ያለው ርብርብ ለሌሎች ሀገሮች እንደማሳያ የሚወሰድ መሆኑን ተናግረው ችግኝ በተከልን ቁጥር ትውልድን ማሻገር ፣ ቋሚ ታሪክን መትከል እንደሆነ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የሀገር ሰላምና ደህንነት ከማስጠበቅ ጎን ለጎን ሀገራችን በምታከናውነው ማንኛውም የልማት ሥራ የሚሳተፍ መሆኑን ያነሱት ምክትል ኮሚሽነር ጀነራሉ በዛሬው ዕለት በመካሄድ ላይ ባለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ የፖሊስ አመራርና አባላት ባሉበት ቦታ ሁሉ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ላይ ተሳትፎ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ስትራቴጅክ አመራሮች እና አባላት፣ በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩንቨርሲቲ ስልጠና እየወሰዱ ያሉ የአማራ ክልል ፖሊስ ስትራቴጅክና ከፍተኛ አመራሮች በዛሬው ዕለት በሰንዳፋ በኬ ከተማ በኬ ጠቦ ቀበሌ በመገኘት ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ችግኝ የተከሉ ሲሆን በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ ቅጥር ግቢ ዙሪያ እና በፎረንሲክ ምርመራና የምርምር ልህቀት ማዕከል ቅጥር ግቢ ውስጥም የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር ማካሄዳቸውን የፖሊስ መረጃ ያመለክታል።