የኢትዮ-ጅቡቲን የባቡር ትራንስፖርት ፍጥነት መጨመር የሚያስችሉ ተጨማሪ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እንደሚከናወኑ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) አስታወቁ።
የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር “የባቡር መሠረተ ልማት ለንግድና ቀጣናዊ ትስስር” በሚል መሪ ሃሳብ እአአ ከ2025 እስከ 2028 የሦስት ዓመታት የስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት በማካሄድ ላይ ይገኛል።
በውይይቱ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር)፥ ዘመናዊ የሎጀስቲክስ አገልግሎት የኢንቨስትመንት ፍሰትን በማሳደግ ለሀገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሁነኛ መሰረት ነው ብለዋል።
በዚህም ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ዕድገት ማስተናገድ የሚያስችል የባቡር፣ የአየር እና የየብስ መንገድ የሎጀስቲክስ ትራንስፖርት አገልግሎት ማዘመን የሚያስችል የለውጥ እርምጃ መወሰዱን አስታውሰዋል።
የኢትዮ-ጅቡቲን የባቡር ትራንስፖርት መስመር ላይ የሚፈጠረውን መስተጓጎል በመቀነስ ፍጥነት መጨመር የሚያስችሉ ተጨማሪ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እንደሚከናወኑ አስታውቀዋል።
በተጨማሪም የኢትዮ-ጅቡቲን የየብስ ትራንስፖርት የመንገድ መሰረተ ልማት ማዘመን የሚያስችሉ ተግባራት በግንባታና በዝግጅት ሂደት ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ሀገራቱን የአፍሪካ የኢኮኖሚ ትብብር ተምሳሌት እንዳደረጋቸውም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የኢትዮ-ጅቡቲን የባቡር መሰረተ ልማት ለማዘመን በሚደረገው ጥረት የልማትና የገንዘብ ተቋማትን የተናበበ ስራና ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ፥ የኢትዮ-ጅቡቲን የምድር ባቡር መሠረተ ልማት ለማዘመን የሚደረገውን ጥረት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
የባቡር መስመሩ በሚያልፍባቸው የከተማና ገጠር አካባቢዎችም የመሠረተ ልማት ደኅንነት መጠበቅ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መሠረተ ልማት በቻይና መንግስት የአንድ መንገድ አንድ ቀበቶ(ቤልት ኤንድ ሮድ ፕሮጀክት) የገንዘብ ድጋፍ መገንባቱም የሶስቱን ሀገራት ስኬታማ የልማት ትብብር የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ፥ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎትን ማጠናከር ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበርን መሠረተ ልማት ዕውን ለማድረግ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ ፈሰስ መደረጉን ተናግረዋል።
የባቡር መሠረተ ልማት ፕሮጀክቱም የኢትዮ-ጅቡትን የልማት ተጠቃሚነት ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ አንስተዋል።
የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ታከለ ዑማ፥ የባቡር መሠረተ ልማቱን የአሰራር ሥርዓት ማዘመን የሚያስችሉ ተግባራት ተከናውነዋል ማለታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በዚህም የአክሲዮን ማኅበሩ የአሰራር ሥርዓት መዘመን ሀገራቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባቸውን ተጠቃሚነት እያሳደገ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት በሚቆየው የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር ከ2025 እስከ 2028 የሦስት ዓመታት የስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ ባተኮረው የፓናል ውይይት ላይ የኢትዮጵያና የጅቡቲ መንግስታት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።