አዲስ አበባን ከቀድሞ ታሪኮቿ ጋር እያጣጣምን ዘመናዊ ከተማ እያደረግናት እንገኛለን ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ

You are currently viewing አዲስ አበባን ከቀድሞ ታሪኮቿ ጋር እያጣጣምን ዘመናዊ ከተማ እያደረግናት እንገኛለን ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ

AMN – ሐምሌ 25/2017 ዓ.ም‎

አዲስ አበባን ከቀድሞ ታሪኮቿ ጋር እያጣጣምን ዘመናዊ ከተማ እያደረግናት እንገኛለን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ።

ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልእክት ዛሬ 4 ኪሎ ፕላዛን፣ 4 ኪሎ የገበያ ማዕከልን እና መኪና ማቆሚያን መርቀን ለአገልግሎት ክፍት አድርገናል ብላዋል።

የአገራችን ብሎም የከተማችን አበይት ታሪካዊ ስፍራ እና የድል ሀውልታችን መገኛ የሆነውን ፣ የተለያዩ ጋዜጦችና መፅሔቶችን ያነበብንበትን፣ እውቀት የቀሰምንበትን፣ ስራ ፍለጋ ማስታወቂያ ለማንበብ የተመላለስንበትን የ4 ኪሎ አደባባይ አካባቢን መልሰን ገንብተን የያዘውን ግዙፍ ታሪክ የሚመጥን፣ ትላንታችንን ከዛሬ እና ከነገአችን ጋር የሚያገናኝ፣ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ፣ ዘመናዊ የከተማ ዲዛይን እና እሴት ያለው ውብ የ4 ኪሎ የገበያ ማዕከልን፣ መኪና ማቆሚያን እና 4 ኪሎ ፕላዛን ገንብተን ለአገልግሎት ክፍት አድርገናል ብለዋል።

ፕሮጀክቱ ከመሬት በታች የተገነቡ እጅግ ዘመናዊ 102 የስጦታ እና የአልባሳት መደብሮች፣ ካፌዎች፣ ካፍቴሪያዎች፣ ማንበቢያ ስፍራዎች፣ ሱፐር ማርኬቶች ፣ ከ100 በላይ ተሽከርካሪዎችን በአንድ ጊዜ የሚያስተናግድ የመኪና ማቆሚያ እና በአንድ ጊዜ እስከ 5 ሺህ ሰዎችን መሰብሰብ የሚያስችል የፕላዛ፣ የአንፊ ቴአትርና የተለያዩ የጥበብ ስራዎችን ማቅረቢያ ስፍራዎችን የያዘ፤ የሲቪል ተሳትፎን፣ የባህል ዕድገትን፣ የእግር ጉዞን የሚያበረታታ፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ፣ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በተለይም አቅመ ደካሞችና አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረገ ነው።

ፕሮጀክቱ ከወዲሁ ከ500 በላይ ለሚሆኑ ወጣቶችና ሴቶች የስራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን፣ የቱሪዝም ፍሰቱን በመጨመር ለዘርፉ ዕድገት የራሱ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልፀዋል ።

ይህ ፕሮጀክት በታለመለት ልክ እንዲጠናቀቅ ድጋፍና ክትትል ስታደርጉ የነበራችሁ ባለ ድርሻ አካላት፣ አመራሮች፣ የአካባቢው ማህበረሰብ በሙሉ ምስጋናዬ ይድረሳችሁ በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review