የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአራት ኪሎ አካባቢ ግንባታቸው የተጠናቀቁ የህዝብ መዝናኛ ፕላዛዎችን፣ የመኪና ማቆሚያ እና የገበያ ማዕከል ፕሮጀክቶችን መርቀው አገልግሎት አስጀምረዋል።
የጀመርነውን እንጨርሳለን የተለምነውን እንፈጽማለን ለህዝብ ቃል ገብተን ጀምረን የማንፈጽመው የለም ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የህዝባችንን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሁሌም እንሰራለን ብለዋል።
የተመረቁት ፕሮጀክቶች 5 ሺህ ሰው ማስተናገድ የሚችል የአራት ኪሎ ፕላዛ፣ ከፕላዘው ስር በመሬት ውስጥ የተገነቡ 33 ሱቆች፣ 100 ተሽከርካሪ በአንድ ግዜ የሚያቆም የተሽከርካሪ ማቆሚያ፣ 75 ሱቆችን እና የታክሲ ተርሚናል የያዘ ከላይ ደግሞ የህዝብ መሰብሰቢያና ምግብ ቤቶች ያሉት ህንጻን ያከተቱ ናቸው።

የምንሰራቸው ልማቶች ትውስታዎቻችንን ጠብቀው ቀድሞ የነበሩ አገልግሎቶችን የሚያሳልጡ እና በተሻለ ደረጃ ጨምሮ ለመስጠት የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል፡፡
በአራት ኪሎ ዙሪያ የተሰሩት የልማት ስራዎችም የጀግኖች አርበኞቻችን መታሰቢያ የሆነውን የድል ሀውልት አካተው በይበልጥ ጎልቶ እንዲታይ የሚያደርጉ፣ ቀድሞ ሲሰጡ የነበሩ የንግድና የትራንስፖርት አገልግሎቶች ልቀው እና ጨምረው እንዲሰጡ የሚያደርጉ፣ እንደ ጋዜጣ እና መጽሄት ማንበቢያ እና መሸጫ የነበሩ የቀድሞ አገልግሎቶች በዘመናዊ መልኩ የተካተቱባቸው መሆናቸውንም ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።
ፕሮጀክቶቹ የከተማዋን የቱሪስት መስህብነት የሚያሳድጉ እንዲሁም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት የሚሰጥባቸው መሆኑም ተገልጿል።
በሰብስቤ ባዩ