አረንጓዴ ዐሻራውን ያሳካነው

You are currently viewing አረንጓዴ ዐሻራውን ያሳካነው

“ሀብታም ስለሆንን ሳይሆን ሀብታም ልብ ያላቸው ዜጎች ስላሉን ነው”

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

በእንግሊዝ ሀገር የሚገኘው ናቹራል ሂስትሪ ሙዚየም (Natural History Museum) የአካባቢ ጉዳዮች ተመራማሪ ፕሮፌሰር አንዲ ፑርቪዝም የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር ያለውን ግንኙነት የተመለከተ ጥናት አካሂደዋል፡፡ ተመራማሪው በጥናታቸው እንደገለጹት፣ የዓለም ህዝብ ቁጥር በእጥፍ ከጨመረበት ከ1970ዎቹ ወዲህ ሰዎች በነፍስ ወከፍ የሚጠቀሙት የምግብ ፍጆታ በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ የሰው ልጅ በተፈጥሮ ላይ እያሳረፈው ያለው ጫና ከፍተኛ ሆኗል፡፡ የሰው ልጆች እስከ አሁን ምድር ላይ በቆዩባቸው ጊዜያትም ቢያንስ 70 በመቶ የሚሆነውን የምድር ክፍል ለራሳቸው ምቾት ሲሉ ቀይረውታል፡፡

ሰዎች እንደዚህ አሟጥጠው አየተጠቀሟት ያለችውን ምድር ግን ለመጠበቅ እያደረጉት ያለው ጥረት የሚያስተዛዝብ ነው የሚሉት ፕሮፌሰሩ፣ “በደን ልማት ስራ በአርዓያነት የሚጠቀሱት ቻይናውያን ‘ምድርን የምትጠብቅበት ከሁሉ የተሻለው ጊዜ ከሃያ ዓመት በፊት ነበር። ሁለተኛው ምርጥ ጊዜ ደግሞ አሁን ነው’ የሚል አባባል እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡ መላው የዓለም ሀገራትም ይህንኑ መርህ እንዲከተሉ ያሳስባሉ፡፡

የችግኝ ተከላን አስቸኳይነት እና ወዲያውኑ እርምጃ የመውሰድን አስፈላጊነትን ለመግለጽ ቻይናውያኑ የተጠቀሙበትን ይህን ድንቅ አባባል የተገነዘቡት እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት ታዲያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሀገርን አረንጓዴ ለማልበስ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የዘንድሮውን የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ባስጀመሩበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት በአረንጓዴ አሻራው ትልቅ ውጤት እየተገኘ መሆኑን አመላክተው፣ “አረንጓዴ ዐሻራውን ያሳካነው ሀብታም ስለሆንን ሳይሆን ሀብታም ልብ ያላቸው ዜጎች ስላሉን ነው” ብለዋል፡፡

አክለውም፣ “ዜጎቻችን ልባቸው ሀብታም፤ አርቆ ማየትን፣ የጋራ ራዕይ መሰነቅን፣ አብሮ መቆምን፣ በጋራ መስራትን፣ በልፋትና በድካም ውስጥ ውጤታማ መሆንን ያውቃሉ፡፡ ዜጎቻችን ይህን ያሳኩት ትርፋማነት ለራስ ብቻ ሳይሆን ለልጆቻችንም ጭምር መሆኑን ማመን ስለቻሉ ነው፤ ለዚህም ነው በአረንጓዴ ዐሻራ ስራ የተሻለ ውጤት ያገኘነው” የሚል ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድ ጀንበር 700 ሚሊዮን ችግኝ የመትከል መርሃ ግብርን በጅማ ባስጀመሩበት ወቅት በሰጡት ማብራሪያ፣ በአንድ ጀንበር ይህን ሁሉ ችግኝ መትከል በጣም ትልቅ እምርታ መሆኑን ገልፀው፣ ይህ ውጤት በዓለም ትልቁ የአንድ ቀን ተከላ ውጤት ነው ብለዋል፡፡ አክለውም፣ “በዚህ ዓመት ወደ 8 ቢሊዮን ገደማ ችግኞች ይተከላሉ። ይህንን ካሳካን በድምሩ 48 ቢሊዮን ችግኝ እንተክላለን ማለት ነው” ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

 “ዕቅዳችን 50 ቢሊዮን መትከል ነው። ለዕቅድ ዘመኑ መጠናቀቅ አንድ ዓመት እየቀረ 48 ቢሊዮን ችግኝ ከተተከለ በቀጣይ ዓመት ከሚከናወነው ተከላ ጋር ከ55 ቢሊዮን በላይ መትከል ተቻለ ማለት ነው፡፡ ይህም ኢትዮጵያ ትልልቅ ነገር ተልማ፣ አቅዳና ህዝቦቿን አስተባብራ ማሳካት እንደምትችል ለእኛም ለሌሎችም ማሳያ ነው” ብለዋል፡፡

የምግብ እጥረት፣ የድህነትና የችግር ምሳሌ ተደርጋ ትወሰድ የነበረችው ኢትዮጵያ አሁን መልኳና ስሟ እየተቀየረ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፣ “ይህ እየሆነ ያለው ሰርተን ነው፡። ጭቃ አብኩተን፣ አፈር ነክተን ነው፡፡ ማንም ይህንን ሊያደርግልን አይችልም፤ እኛው ሰርተን፣ ምግባችንን በጓሯችን አምርተን ኢትዮጵያን ከችግር ማውጣት አለብን፤ ይህን ማድረግ የዜጎቿ ኃላፊነት ስለሆነ በመጀመሪያ ችግሩን (የድሃ ሀገር ዜጎች መሆናችንን) አምነን መቀበል፣ መስማማት፣ አንድ የጋራ ራዕይ መሰነቅ፣ ራዕዩን ለማሳካት ደግሞ በጋራ መረባረብ ነበር የሚጠበቅብን፤ አካሄዳችን ተስፋ ሰጪ ነው፤ ዘንድሮ በታቀደው መሰረት እየተከናወነ ነው ያለው” የሚል ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በዘንድሮው የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከ714 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ችግኞች መትከል መቻሉን ልብ ይሏል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ምድርን አረንጓዴ ማልበስ የሚኖረውን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አስመልክቶ እ.ኤ.አ በ2023 ይፋ ባደረገው መረጃ፣ የአረንጓዴ ልማት የተለያዩ የዕፅዋት ዝርያዎች በአንድ ስፍራ እንዲለሙ በማድረግ ልዩ ልዩ የእንስሳት ዝርያዎች በምቾት የሚኖሩበትን ዕድል ይፈጥራል፤ ይህም ብዝሃ ሕይወት እንዲኖር ያደርጋል። ፓርኮች፣ መናፈሻዎች እና አረንጓዴ ኮሪደሮች የዱር አራዊትን የሚደግፉ እና ዝርያዎችን ለመጠበቅ የሚያበረታቱ የስነ-ምህዳር መረቦችን ይፈጥራሉ ይላል።

በአረንጓዴ ልማት ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎችን ያስገኛል የሚለው መረጃው፣ አረንጓዴ ቦታዎች የንብረት እሴቶችን ይጨምራሉ፣ ቱሪስቶችን ይስባሉ፣ ጤናማ የአኗኗር ዘይቤዎችን በማስተዋወቅም ለህክምና የሚውለውን በርካታ ገንዘብ፣ ጉልበትና ጊዜ በመቀነስ ሀገራት አቅማቸውን በሌሎች ልማቶች ላይ እንዲያውሉ ዕድል ይሰጣል፡፡

የደን ልማትና የደን ምርቶች ለሀገራዊ ኢኮኖሚ ያላቸውን አስተዋጽኦ በተመለከተ በርካታ ጥናቶች ተካሂደዋል። እነዚህ ጥናቶች የደን ልማት ስራ እንደ እንጨት፣ ፍራፍሬ፣ ማር፣ መድኃኒትነት ያላቸው ዕፅዋት፣ ለእንስሳት መኖነት የሚያገለግሉ ምርቶችን ለማግኘት እንደሚያግዝ ያብራራሉ፡፡ እንደዚሁም የገቢ ምንጭነት፣ ለውጭ ምንዛሪ ማስገኛነት እና ለጥቅል ሀገር ውስጥ ምርት (GDP) ዕድገት ፋይዳ እንዳላቸውም ይጠቁማሉ፡፡

በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ዙሪያ ከዚህ ቀደም ለአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ሙያዊ ማብራሪያ የሰጡት የአዲስ አበባ  ዩኒቨርሰቲ የእፅዋት ኢኮሎጂ  እና ብዘሃ ህይወት  ተባባሪ  ፕሮፌሰር ገመዶ ዳሌ (ዶ/ር)ዓለም በተለይ ባለፉት 50 ዓመታት ሰዎች የሚፈልጉትን የማቅረብ አቅሟ እየተሟጠጠ መምጣቱን ጠቅሰው፣ ሰዎች ለአካባቢያቸው በቂ ጥበቃ እያደረጉ ባለመሆናቸው የደን መጨፍጨፍ፣ የመሬት መራቆትን፣ የብዝሃ ህይወት መጥፋትና ብክለትን እንድንጋፈጥ ሆነናል ይላሉ፡፡

ዛፎች የአፈር ለምነትን በማሻሻል፣ ውሃ በመያዝ እና የአየር ንብረትን በማስተካከል የግብርና ምርቶችን ለማሳደግ ይረዳሉና የችግኝ ተከላ ስራ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ የሚገባው ጉዳይ ስለመሆኑም አስረድተዋል። ዛፎች ንፁህ አየር የሚሰጡን፣ በነጻ የሚንከባከቡን ጸጋዎቻችን በመሆናቸው እያንዳንዱ ሰው ባለው አካባቢ አንድ ዛፍ መትከልና መንከባከብ ይኖርበታል፡፡ ይህን ሲያደርግ ቤተሰቡንና አካባቢውን ተንከባከበ ማለት ነው ሲሉም ይመክራሉ፡፡

ገመዶ ዳሌ (ዶ/ር) ቻይናን በአብነት በማንሳት በአረንጓዴ ልማት ስራዋ ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ በማድረግ እና ሰፋፊ ፕሮጀክቶችን በመተግበር በርካታ ጥቅሞችን እንዳገኘች ይገልጻሉ። ሀገሪቱ ደንን በማልማቷ ተጠቅማለች ያሏቸውን ጉዳዮች ሲዘረዝሩም የደን ሽፋን መጨመር፣ የካርቦን ልቀትን መቀነስ፣ የአየርና ውሃ ጥራት መሻሻል፣ የኢንዱስትሪ ልማት፣ የስራ ዕድል ፈጠራና የህዝብ ጤና መሻሻልን ከብዙ በጥቂቱ መጥቀስ ይቻላል፡፡

ቻይና በታዳሽ ኃይል ላይ ባደረገችው ከፍተኛ የገንዘብ ወጪ የካርቦን ልቀትን በመቀነስ ረገድ ትልቅ እመርታ አሳይታለች። እ.ኤ.አ በ2024 ከዓለም አቀፍ ታዳሽ ኃይል አቅም ውስጥ ከ40 በመቶ በላይ የሚሆነውን ድርሻ የያዘች ሲሆን፣ እ.ኤ.አ በ2022 ደግሞ በታዳሽ ኃይል ምርት ወደ 2 ነጥብ 26 ቢሊዮን ቶን ካርቦን ዳይኦክሳይድ ልቀትን ቀንሳለች።

ልክ እንደ ቻይና ሁሉ ኢትዮጵያም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ባከናወነችው የደን ልማት ስራ በርካታ ስኬቶችን አስመዝግባለች፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት የኢትዮጵያ የደን ሽፋን የአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄ በተጀመረበት ወቅት (በ2011 ዓ.ም) ከነበረበት 17 ነጥብ 2 በመቶ አሁን ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ ማለት ችሏል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በማብራሪያቸው፣ በአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከ20 እስከ 30 ሚሊዮን የሚደርስ ህዝብ እንደሚሳተፍ (በዘንድሮው የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ብቻ 29 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሰዎች መሳተፋቸውን ልብ ይሏል) ጠቁመው፣ በዚህ አስደናቂ ስራም ኢትዮጵያ ያሰበችውን ማሳካት እንደመትችልና የአረንጓዴ ዐሻራው ልክ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን ትልቅ የዐሻራ አካል ነው ብለዋል፡፡ አክለውም፣ በዚህም አትርፈናል፤ በቡና፣ በሻይ፣ በፍራፍሬና አትክልት ቀላል ያልሆነ ትርፍ አግኝተናል በማለት አብራርተዋል፡፡

“ይህ ታላቅ ዓላማ እንዲሳካ በረደን፣ ሰለቸን ሳይሉ በብርድ እና በዝናብ ሳይበገሩ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ዜጎች ምስጋና ይገባቸዋል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ “ጀምረናል እንጨርሳለን፤ ተልመናል እናሳካለን፤ ድሃ ነበርን እንበለፅጋለን፤ የኢትዮጵያ ስም፣ መልክና ታሪክ ይቀየራል፤ የዚህ ታሪክ አካል መሆን መታደል ስለሆነ ሁላችንም ዕድሉ እንዳያመልጠን እንበርታ” የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ 

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review