የ4 ኪሎ ፈርጦች

You are currently viewing የ4 ኪሎ ፈርጦች

   “አዲስ አበባን ከቀድሞ ታሪኮቿ ጋር እያጣጣምን ዘመናዊ ከተማ እያደረግናት እንገኛለን”                     

                           የአዲስ አበባ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ ትናንትን የምታስታውስ ታሪካዊ መዲና፣ ዘመናዊነትን ያቀፈች የዛሬ ከተማ እና የወደፊቱን ከግምት ያስገባች ማዕከል ሆና ብቅ እያለች ነው። ባለፉት ጥቂት ዓመታት በከተማዋ እየተሰሩ ያሉ መጠነ ሰፊ የልማት ስራዎች ታሪካዊነቷን ጠብቀው፤ ገጽታዋን እየቀየሩት ነው። ይህ ደግሞ አዲስ አበባ ለነዋሪዎቿ ምቹ እና ጽዱ እንድትሆን ከማድረጉም ባሻገር በዓለም አቀፍ ደረጃ ይበልጥ ማራኪና ተወዳዳሪ እንድትሆን እያደረጋት ይገኛል።

በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የዘመናዊ ከተማ ግንባታዎች ብዙ ናቸው። ከፍታ ያላቸው ሕንፃዎች፣ ሰፋፊ መንገዶች፣ ዘመናዊ የመብራትና የትራንስፖርት መሠረተ ልማቶች ደረጃዋን ከፍ እያደረጉት ይገኛል። የከተማዋን ውበት የሚጨምሩት የአረንጓዴ ልማት ፕሮጀክቶችም የዘመናዊቷ አካል ሆነዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዋና ዋና መንገዶችና በአደባባዮች ዙሪያ የተተከሉት ዛፎች እና አበባዎች ለከተማዋ አዲስ ገጽታ እና ውበትን ሰጥተዋታል። ከመሬት በታች የተሰሩ የእግረኛ መንገዶች፣ የመኪና ማቆሚያ ቦታዎች፣ የንግድ ማዕከላትና ሌሎች ፕሮጀክቶች ደግሞ መዲናዋን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንድትሆን ስንቅ የሚሆኗት መገለጫዎቿ ናቸው፡፡ ለአብነት በትናንትናው እለት የተመረቀው 4 ኪሎ ፕላዛ፣ 4 ኪሎ የገበያ ማዕከል እና መኪና ማቆሚያ ለመዲናዋ ትልቅ የኢኮኖሚ አቅም ለመፍጠር አጋዥ አቅም ከመሆናቸውም ባሻገር ተጨማሪ ውበትንና ምቹነትን የሚሰጡ፣ አዲስ ገጽታንም የሚያላብሱ ናቸው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የፕሮጀክቱ ስራ መጀመርን አስመልክተው በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጹሑፍ፣ አዲስ አበባን ከቀድሞ ታሪኮቿ ጋር እያጣጣምን ዘመናዊ ከተማ እያደረግናት እንገኛለን ብለዋል።

ከንቲባዋ የሀገራችን ብሎም የከተማችን አበይት ታሪካዊ ስፍራ፣ የድል ሀውልታችን መገኛ፣ የተለያዩ ጋዜጦችና መፅሔቶችን ያነበብንበትን፣ እውቀት የቀሰምንበትን፣ ስራ ፍለጋ ማስታወቂያ ለማንበብ የተመላለስንበትን የ4 ኪሎ አደባባይ አካባቢን መልሰን ገንብተን የያዘውን ግዙፍ ታሪክ የሚመጥን፣ ትላንታችንን ከዛሬ እና ከነገአችን ጋር የሚያገናኝ፣ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ፣ ዘመናዊ የከተማ ዲዛይን እና እሴት ያለው ውብ የ4 ኪሎ የገበያ ማዕከልን፣  መኪና ማቆሚያን እና 4 ኪሎ ፕላዛን ገንብተን ለአገልግሎት ክፍት አድርገናል ሲሉም አክለዋል።

ፕሮጀክቱ ከመሬት በታች የተገነቡ እጅግ ዘመናዊ 102 የስጦታ እና የአልባሳት መደብሮች፣ ካፌዎች፣ ካፍቴሪያዎች፣ ማንበቢያ ስፍራዎች፣ ሱፐር ማርኬቶች፣ ከ100 በላይ ተሽከርካሪዎችን በአንድ ጊዜ የሚያስተናግድ  የመኪና ማቆሚያ እና  በአንድ ጊዜ እስከ 5 ሺህ ሰዎችን መሰብሰብ የሚያስችል የፕላዛ፣ የአንፊ ቴአትርና የተለያዩ የጥበብ ስራዎችን ማቅረቢያ ስፍራዎችን የያዘ፤ የሲቪል ተሳትፎን፣ የባህል ዕድገትን፣ የእግር ጉዞን የሚያበረታታ፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ፣ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በተለይም አቅመ ደካሞችና አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረገ ነው።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደገለጹት፣ ፕሮጀክቱ ከወዲሁ ከ500 በላይ ለሚሆኑ ወጣቶችና ሴቶች የስራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን፣ የቱሪዝም ፍሰቱን በመጨመር ለዘርፉ ዕድገት የራሱ ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ 

በእርግጥም አዲሱ 4 ኪሎ ፕላዛ፣ 4 ኪሎ የገበያ ማዕከል እና መኪና ማቆሚያ የአዲስ አበባ የትናንት ታሪክ ከዘመናዊነት ጋር የተጣጣመበትና ለወደፊቱ ትውልድም ትልቅ ትርጉምና ጥቅም እንዲሰጥ ተደርጎ የተሰራ ነው፡፡ ይህ አይነቱ ስራ ቀጣዩ ትውልድ ከታሪኩ ጋር ትስስር እንዲኖረው፣ ታሪኩን እያወቀና እየኮራበት ከዘመናዊው ዓለም ጋር እንዲራመድ ይረዳል። የከተማዋ ለውጥ የሚያሳየው፣ ያለፈ ታሪክን ሳይዘነጉ እንዴት ወደፊት መሄድ እንደሚቻል ነው። ይህም የኢትዮጵያ መዲና፣ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እና የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችው አዲስ አበባን ከትልልቅ ከተሞች ጋር ተወዳዳሪና ምቹ የሚያደርጋት ነው፡፡

ሞላ አለማየሁ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የኢኮኖሚክ አሶሴሽን ከፍተኛ ተመራማሪ ናቸው፡፡ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት አስተያየት፣ “አንዲት ከተማ ምቹ ለመባል መሰረታዊ የሆኑ አገልግሎቶችን ማሟላት አለባት፡፡ እንዲሁም ከመሰረታዊ ፍላጎት በተጨማሪ ነዋሪዎች የተሻለ  የሚዝናኑበትን መሰረተ ልማት ማሟላት ይኖርባታል፡፡ በአጠቃላይ ዜጎች የሚፈልጉትን መሰረተ ልማት በበቂ ሁኔታና በጥራት ማቅረብ የምትችል ከተማ ለኑሮ ምቹ ነች ተብሎ ይታሰባል” ይላሉ፡፡

ከዚህ አንጻር በአዲስ አበባ የተጀመሩ ስራዎች ተስፋ ሰጪ እንደሆኑ አንስተዋል፡፡ እነዚህን ልማቶች በማስፋትና አቅምን በማሳደግ መዲናዋን ህዝቡ በሚፈልገው ልክ ምቹ ከማድረግ አንጻር ከዚህም በላይ መስራት እንደሚያስፈልግ አክለዋል፡፡

በትናንትናው እለት በከንቲባ አዳነቼ አቤቤ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት የሆነው የ4 ኪሎ ፕላዛ፣ 4 ኪሎ የገበያ ማዕከል እና መኪና ማቆሚያ በካናዳዋ ቶሮንቶ ከተማ ከተሰራው “Path Underground Shopping Mall”፣ በደቡብ ኮሪያዋ ጄጁ ከተማ ከሚገኘው “Jeju Jungang Underground Shopping CenterÈ፣ በኦስትሪያዋ ሳልዝበርግ ከሚገኘው Çthe Mönchsberg garageÈ እንዲሁም  በጃፓኖቹ ቶክዮ እና ኦሳካ ከመሬት በታች ከሚገኘው ፕሮጀክቶች ጋር የሚወዳደር ነው፡፡

የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት ምሁሩ ፋሲል ጣሰው ፕሮጀክቶቹን አስመልክተው በቅርቡ ለአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በሰጡት አስተያየት፣ እንደ ቻይና እና ጃፓን ባሉ ሀገራት ረጅም ኪሎ ሜትሮችን የሚጓዙ፣ ከተሞችን እርስ በእርስ የሚያገናኙ የባቡር መስመሮች በመሬት ውስጥ መዘርጋታቸው የደረሱበትን ደረጃ ያመላክታል፡፡ ይህ ልምድ በእኛም ሀገር፤ በተለይ አዲስ አበባ ከተማ የ4 ኪሎ ፕላዛን ጨምሮ በሌሎች ፕሮጀክቶች እየተጠናከረ መምጣቱ ይበል የሚያሰኝ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

እንደሳቸው ገለፃ፤ በመሬት ውስጥ ያለን ቦታ ለተለያየ አገልግሎት በሚውል አግባብ ማልማት ውስን የሆነውን ሃብት በተሻለ ደረጃ (እሴት ጨምሮ) ለመጠቀም ያስችላል፡፡ በውስን የመሬት ይዞታ ላይ በርካታ ዜጎችን የሚጠቅም መሰረተ ልማት ለአገልግሎት ለማብቃት ዕድል ይፈጥራል፡፡ በከተማዋ የሚታየውን የትራፊክ መጨናነቅ፣ የማምረቻ እና የመሥሪያ ቦታ እጥረት ያቃልላል፡፡ ለዜጎች የሥራ ዕድልን ይፈጥራል፡፡ ራስን፣ ቤተሰብንና ሀገርን ሊለውጡ የሚችሉ ሃሳቦችን መጋራት የሚያስችሉ ሁነኛ አካባቢዎች ሆነውም ያገለግላሉ፡፡ ስለዚህ የ4 ኪሎ ፕላዛን ዓይነት የመሬት ውስጥ መሰረተ ልማቶችን ያካተቱ ፕሮጀክቶች መስፋፋት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡ ከተማ አስተዳደሩ እነዚህን ዓይነት የልማት ሥራዎች አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበት በመጠቆም፤ በቀጣይ የሚሠሩት ሥራዎች ከዚህም በላይ ስፋት ያላቸው፣ በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ፣ ዘላቂነታቸውም በጥናት የተረጋገጠ መሆን እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡

የአንድ መስኮት አገልግሎት የሚባሉ አሰራሮች በመላው አለም እየተለመዱ መጥተዋል የሚሉት ሞላ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የአራት ኪሎ ፕሮጀክቶች ንግድ ያቀላጥፋሉ፡፡ ጊዜን ይቆጥባሉ፡፡ የስራ እድል ይፈጥራሉ፡፡ ሻጭና ገዥን በአንድ ያገናኛሉ፡፡ የኑሮ ደረጃን ያሻሽላሉ፡፡ ምክንያቱም ብዙ አገልግሎቶችን በአንድ የያዘ ማእከል ነው፡፡ ስለዚህ ከተማዋን ምቹ ከማድረግ በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውም ከፍተኛ ነውና ወደ ሌሎች ቦታዎች መስፋፋት እንዳለባቸው አብራርተዋል፡፡

በጊዜው አማረ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review