ተለዋዋጭ ነባራዊ ሁኔታዎችንና ሀገራዊ አቅጣጫዎችን ታሳቢ ያደረገ የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ሥራ በበጀት ዓመቱ ትኩረት እንደሚሰጠዉ ለገሠ ቱሉ(ዶ/ር) ገለጹ

You are currently viewing ተለዋዋጭ ነባራዊ ሁኔታዎችንና ሀገራዊ አቅጣጫዎችን ታሳቢ ያደረገ የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ሥራ በበጀት ዓመቱ ትኩረት እንደሚሰጠዉ ለገሠ ቱሉ(ዶ/ር) ገለጹ

AMN ሐምሌ 26/2017 ዓ.ም

ተለዋዋጭ ነባራዊ ሁኔታዎችንና ሀገራዊ አቅጣጫዎችን ታሳቢ ያደረገ የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ሥራ በበጀት ዓመቱ ትኩረት እንደሚሰጠዉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚንስትር ለገሠ ቱሉ (ዶ.ር) ገለጹ።

የአገልግሎቱ የ2018 በጀት ዓመት የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዕቅድ ላይ ውይይቶች ተደርገዋል።

በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ አቅጣጫ ያስቀመጡት ዶ.ር ለገሠ ” ነባራዊ ኹኔታዎችን መሠረት አድርጎ የኢትዮጵያን ማንሠራራት ማጽናት ላይ ያተኮረ የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ሥራ ትኩረት ይሰጠዋል” ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ የዘርፉ ዕቅድ ትኩረት ሊያደርግባቸዉ የሚገባ ጉዳዮች ላይም ክቡር ሚንስትሩ አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡

የመንግሥትን መረጃ፣ ዕቅድ፣ አፈጻጸምና ውጤት ለምልዓተ ሕዝቡ መረጃዎችን ተደራሽነት ለማድረግ ልዩ ትኩረት እንደሚደረግም ተመላክቷል።

በመንግሥት የተያዙ ፕሮጀክቶችን ሂደት፣ ፋይዳ እና የምልዓተ ሕዝቡን ተሳትፎ ማጎልበትም በትኩረት ይሠራባቸዋል።

ሰላምን ማጽናት፣ ስጋቶችን ቀድሞ መለየትና መተንተን፣ ልዩ ልዩ ተነሣሽነቶችን ማስረጽ፣ ብዝኃ ኢኮኖሚውንና ሪፎርሙን ማስገንዘብና ምልዓተ ሕዝቡን ማሳተፍ የአገልግሎት ዕቅድ ያተኮረባቸው ይዘቶች ቸው።

የመንግሥት ኹለንተናዊ የመፈጸም ዐቅም ማደግ፣ የፕሮጀክቶች አፈጻጸም በከፍተኛ ደረጃ መሻሻል፣ የሪፎርም ሥራዎች ያስመዘገቧቸው ስኬቶች እና በዲፕሎማሲ መስክ የተመዘገቡ ድሎች ለዘርፉ ሥራ መሠረቶች መኾናቸዉን ሚንስትሩ አመላክተዋል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚንስትር ዲኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ ደግሞ በቀጣይ በሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ የሚሰራጩ ሐሰተኛ መረጃዎችን የማጋለጥ እና የመሞገት ሥራ በልዩ ትኩረት እንደሚሠራ አስታውቀዋል፡፡

በሀገሪቱ ሰላምና ፀጥታ፣ በኢኮኖሚ ዕድገት እና በአንኳር የልማት ሥራዎች ላይ የተመዘገቡ ውጤቶችን ለማጥላላት የሚሰራጩ አሉታዊ መረጃዎችን በትክክለኛ አኀዞች ተመሥርቶ ማረም፣ ቀድሞ ተንባይ የኮሙኒኬሽን አቅጣጫን በመከተል የአጀንዳ ብልጫ ለመውሰድ በቁርጠኝነት እንደሚሠራም አቶ ተስፋሁን ተናግረዋል፡፡

ለኹለት ቀናት ሲካሄድ የነበረው በ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም እና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ያተኮረዉ ውይይት መጠናቀቁን ከመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ያገኘነዉ መረጃ ያሳያል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review