የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዘንድሮውን ተቋማዊ የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት በይፋ በድሬዳዋ ከተማ ጀመረ

You are currently viewing የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዘንድሮውን ተቋማዊ የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት በይፋ በድሬዳዋ ከተማ ጀመረ

AMN – ሐምሌ 26/2017 ዓ.ም

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዘንድሮውን ተቋማዊ የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት በይፋ በድሬዳዋ ከተማ ጀምሯል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዋናው መሥሪያ ቤት ፣ከሚሲዮኖች እና ከተጠሪ ተቋማት በማሰባሰብ በድሬደዋ ከተማ ለሚገኙ ድጋፍ ለሚሹ 500 ተማሪዎች የትምህርት መማሪያ ቁሳቁስ እና መርጃ መሣሪያዎችን አበርክቷል።

በተያያዘም በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስተባባሪነት በድሬደዋ ከተማ 20 የአቅመ ደካማ ሰዎች መኖሪያ ቤቶችን ገንብቶ ለማስረከብ ዛሬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታዎች አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ፣ አምባሳደር ሃደራ አበራ እንዲሁም በኬንያ የኢትዮጵያ ባለሙሉሥልጣን አምባሳደር ባጫ ደበሌ እና የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በተገኙበት የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል።

በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሃደራ አበራ፣ በጎ ሥራ እና በጎ ፈቃድ አገልግሎት ዋነኛ የሰብአዊነት መገለጫ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ገልጸዋል።

አምባሳደሩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እና ሥራ የወገን አለኝታነት መገለጫ ጭምር መሆኑን አንስተዋል።

በኬንያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር የሆኑት አምባሳደር ባጫ ደበሌ በበኩላቸው ለእንዲህ አይነት ሥራ መመረጥ መታደል እና ትልቅ ኃላፊነት ነው ብለዋል።

አምባሳደር ባጫ ሚሲዮናቸው ለበጎ ምግባር የሚተጉ ሰዎችን በማሰባሰብ 20 የአቅመ ደካማ ሰዎች መኖሪያ ቤቶችን የምሥራቋ ኮከብ እና የፍቅር ከተማ በሆነችው ድሬደዋ የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጥ መቻላቸው የፈጠረባቸውን ልዩ ስሜት ገልጸዋል።

አምባሳደሩ ይህ እቅድ የተሳካ እንዲሆን አስተዋጽኦ ላደረጉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ለድሬደዋ ከተማ አስተዳደር አመራሮች ምስጋና ማቅረባቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review