የኢትዮጵያ አየር መንገድ አራተኛውን ኤርባስ A350-1000 አውሮፕላን ዛሬ መረከቡን አስታወቀ።
አውሮፕላኑ ለደንበኞች የላቀ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ቴክኖሎጂ የተገጠመለት መሆኑንም ገልጿል።
A350-1000 አውሮፕላን ከ350 እስከ 410 መንገደኞችን የመያዝ አቅም ያለው ነው።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኤርባስ A350-1000 አራት አውሮፕላኖችን ለመግዛት አዞ የነበረ ሲሆን የመጨረሻውን አውሮፕላን ዛሬ መረከቡን ለኢዜአ በላከው መረጃ አስታውቋል።
አየር መንገዱ የተረከበው A350-1000 አውሮፕላንም በአይነቱ ልዩና በአፍሪካ የመጀመሪያው ነው።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጥቅምት 26 ፤2017 ዓ.ም በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን A350-1000 የመንገደኞች አውሮፕላን የተረከበ ሲሆን አውሮፕላኗን ”Ethiopia land of origins” በሚል ሰይሞታል። ይህም የኢትዮጵያን ቱሪዝም መስህብ ከማስተዋወቅ ጋር የተገናኘ ነው።
አውሮፕላኑ የመጀመሪያ በረራውን ጥቅምት 26፤ 2017 ዓ.ም ወደ ናይጄሪያዋ ሌጎስ ከተማ ማድረጉ አይዘነጋም።
አየር መንገዱ በአሁኑ ሰዓት ባሉት ከ160 በላይ አውሮፕላኖች ከ140 በላይ ዓለም አቀፍና 22 የሀገር ውስጥ የበረራ መዳረሻዎችን እየሸፈነ ይገኛል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ እ.አ.አ በ2035 ዓመታዊ ገቢውን ወደ 25 ቢሊዮን ዶላር ከፍ በማድረግና በዓመት 67 ሚሊዮን መንገደኞችን ለማጓጓዝ ራዕይ ሰንቆ እየሰራ ይገኛል።