የአፍሪካ የድህረ ምርት ቅነሳ ጉባኤ እና አውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

You are currently viewing የአፍሪካ የድህረ ምርት ቅነሳ ጉባኤ እና አውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

AMN ሐምሌ 27/2017

አምስተኛው የአፍሪካ የድህረ ምርት ብክነት ቅነሳ ጉባኤ እና አውደ ርዕይ ከመስከረም 6 እስከ 9 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

በሁነቱ ከ400 በላይ ልዑካን እንደሚሳተፉም ተገልጿል።

ኢትዮጵያ በቅርቡ ሁለተኛውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምግብ ስርዓት ጉባኤ በስኬት ማስተናገዷ ይታወቃል።

የአፍሪካ የድህረ ምርት ቅነሳ ጉባኤ እና አውደ ርዕይ “ ምርትን መጠበቅ፤ የድህረ ምርት ብክነት አስተዳደር መፍትሄዎች ለማይበገር እና ሁሉን አካታች የምግብ ስርዓት” በሚል መሪ ሀሳብ ይካሄዳል።

ጉባኤው በአፍሪካ የድህረ ምርት ብክነትን በፍጥነት መቀነስ እንዲሁም ዘላቂ የግብርና እና የምግብ ስርዓቶችን ማጠናከር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ እንደሚመክር ኢዜአ ከአፍሪካ ህብረት ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

የምግብ ብክነት እና አወጋገድ አፍሪካ ዜጎቿን በራሷ የመመገብ አቅሟን እየፈተነው እንደሚገኝ ህብረቱ ገልጿል።

ደካማ የድህረ ምርት ብክነት ቅነሳ ስራዎች፣ የምግብ ማከማቻዎች በበቂ ሁኔታ አለመኖር እና የትራንስፖርት አገልግሎት አለመሟላት አፍሪካ ውስጥ ከሚመረተው ምግብ 13 ነጥብ 2 በመቶ ተጠቃሚ ጋር ሳይደርስ እንደሚባክን ምክንያት እንደሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የአፍሪካ ህብረት ይሄን ችግር በተቀናጀ አሰራርና በባለድርሻ አካላት ትብብር በጠንካራ ምላሽ ለመፍታት እየሰራ እንደሚገኝ አመልክቷል።

አህጉራዊው ጉባኤ በቅርቡ ይፋ ከተደረገው የአፍሪካ ሁሉን አቀፍ የግብርና ልማት ፕሮግራም(ካዴፕ) የካምፓላ ድንጋጌ ጋር የተጣጣመ መሆኑ ተገልጿል።

በዚሁ ድንጋጌ ላይ እ.አ.አ በ2035 በአፍሪካ የድህረ ምርት ብክነትን በ50 በመቶ ለመቀነስና ለገበያ የሚቀርቡ የግብርና ምርቶችን በ45 በመቶ የመጨመር እቅድ ተይዟል።

በጉባኤው ድህረ ምርትን የተመለከቱ የተለያዩ ውይይቶች የሚደረጉ ሲሆን የምርምር ውጤቶች እንደሚቀርቡና የተለያዩ የጎንዮሽ ሁነቶችና አውደ ርዕዮች እንደሚካሄዱ የህብረቱ መረጃ ያመለክታል።

ወጣቶችና ሴቶች ድህረ ምርት ብክነትን የሚቀንሱ ስርዓቶችን ከመዘርጋት አኳያ ያላቸው ሚና ከጉባኤው የትኩረት ማዕከል መካከል ይጠቀሳል።

አርሶ አደሮች፣ ተመራማሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ባለሀብቶች እና የሲቪክ ማህበረሰብ ተቋማትን ጨምሮ ከ400 በላይ ልዑካን በጉባኤው ላይ ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ተሳታፊዎች የእውቀት እና የቴክኖሎጂ ልምድ ልውውጥ ከማድረጋቸው ባሻገር አፍሪካ የማይበገር ጠንካራ የምግብ ስርዓት መገንባት በምትችልበት ሁኔታ ላይ ይመክራሉ።

የድህረ ምርት ብክነት ቅነሳ እና ጠንካራ ስርዓተ ምግብ ግንባታን አስመልክቶ የጋራ አቋም መግለጫ እንደሚወጣም ይጠበቃል።

ጉባኤው እና አውደ ርዕዩ አፍሪካ የምግብ ሉዓላዊነትን እና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ያላትን ቁርጠኝነት እንደሚያመላክት ህብረቱ ገልጿል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ከልማት አጋሮች፣ ከትምህርት ዘርፍ ተዋንያንና የግሉ ዘርፍ ጋር በመሆን አህጉራዊውን ጉባኤ ያዘጋጃል።

ኢትዮጵያ ከሐምሌ 20 እስከ 22 ቀን 2017 ዓ.ም ሁለተኛውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምግብ ስርዓት ጉባኤ በስኬት ማስተናገዷ ይታወቃል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review