የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በዉጪ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት ገንዘባቸዉን አስተማማኝ እና ህጋዊ በሆኑ ተቋማት ብቻ ለሚወዷቸዉ መላክ እንደሚገባቸዉ አሳስቧል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ይህንኑ ጉዳይ አስመልክቶ በውጭ ለሚኖሩ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት የጥንቃቄ መልእክት አስተላልፏል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ እንዳስታወቀዉ ድንበር ተሻጋሪ የሆኑ ገንዘብ የማስተላለፍ ግብይቶች መከናወን ያለባቸዉ በመደበኛ እና ቁጥጥር በሚደረግበት የፋይናንስ አማካኝነት ብቻ መሆን እንዳለበት ገልጿል፡፡
ይህም ተገቢ የሆነ የቁጥጥር ስርዓትን ለማስፈንና በወንጀል የተገኘ ንብረት ህጋዊ የማስመሰል እንዲሁም ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ተጋላጭነትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ወሳኝ ሚና እንዳለዉ አስታዉቋል፡፡
ነገር ግን ከዚህ መርህ ባፈነገጠ መንገድ እንዲሁም የኢትዮጵያን የፋይናንስ ስርዓት ታማኝነት ሆነ ብለዉ ለመሸርሸርና የገበያን ዋጋ ለማዛባት በማለም መቀመጫቸዉን በአሜሪካ ሃገር ያደረጉ የተለያዩ ገንዘብ ማስተላለፍ አገልግሎት ሰጪዎች በዉጪ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ በሚሰበስቡት ገንዘብ አማካኝነት በወንጀል የተገኘ ንብረትን ህጋዊ የማስመሰል እና ህገ ወጥ ተግባራትን ፋይናንስ በማድረግ ተግባር እንደተሳተፉ ተደርሶባቸዋል ሲል የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ አስታዉቋል፡፡
እነዚህ ተቋማትም
1ኛ. ሸገይ ገንዘብ አስተላላፊ- Silver Spring, MD and Falls church, VA, USA
2ኛ. አዱሊስ ገንዘብ አስተላላፊ- Falls church, VA, and Silver Spring, MD,USA
3ኛ. ራማዳ ፔይ (ካህ) – Falls church ,VA,USA
4ኛ. ታጅ ገንዘብ አስተላላፊ – Minneapolis ,MN, USA መሆናቸዉን ይፋ አድርጓል፡፡
እነዚህ ተቋማት በሚገኙበት ያሉ አግባብነት ያላቸዉ የህግ አስፈጻሚ አካለት ትብብር እንዲያደርጉና ምርመራ እንዲያከናዉኑ ጥያቄ መቅረቡን ገልጿል፡፡
በመሆኑም በዉጪ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት ከነዚህ ተቋማት ጋር ያላቸዉን ግንኙነት እንዲያቆሙና ገንዘባቸዉ አስተማማኝ እና ህጋዊ በሆኑ ተቋማት ብቻ ለሚወዷቸዉ መላኩን እንዲያረጋግጡ አጥብቀን እንመክራለን ሲል ባንኩ የጥንቃቄ መልእክቱን አስተላልፏል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ እያከናወነ ያለዉን ምርመራ በመቀጠል እንደአስፈላጊነቲ ተገቢ እርምጃዎችን በቀጣይ የሚወስድ መሆኑንም ጨምሮ ገልጿል፡፡
በነዚህ ተቋማት አማካኝነት የሚላክ ገንዘብ በወንጀል የተገኘ ንብረትን ህጋዊ ከማስመሰል ድርጊት ጋር በተያያዘ ምክንያት ሊወረስ የሚችል መሆኑን እና በዚህ አግባብ የተላከዉ ገንዘብ ለታለመለት ተቀባይ የሚደርስ ስለመሆኑ ዋስትና አለመኖሩን በመገንዘብ ህብረተሰቡ በነዚህ ተቋማት አማካኝነት ገንዘብ ከማስተላለፍ እንዲታቀብ ብሄራዊ ባንክ አበክሮ አሳስቧል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ቀጥሎ በተመለከተዉ ሊንክ (https://nbe.gov.et/mta/) ፈቃድ ያላቸው እና አግባብነት ባላቸው ህጎች መሰረት የገንዘብ ማስተላለፍ አገልግሎት ሰጪ ሆነው በገበያው ውስጥ እንዲሰሩ የተፈቀደላቸውን የሁሉንም ተቋማት የተሟላ ዝርዝር ማካተቱን በማህበራዊ ትስስሩ ገጹ ይፋ አድርጓል፡፡