የከተማና ገጠር የኮሪደር ልማት ለዜጎች ተጠቃሚነት ምቹ ምኅዳር እየፈጠሩ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ

You are currently viewing የከተማና ገጠር የኮሪደር ልማት ለዜጎች ተጠቃሚነት ምቹ ምኅዳር እየፈጠሩ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ

AMN ሐምሌ 27/2017

በከተሞችና በገጠር እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ለዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ምቹ ምኅዳር እየፈጠሩ እንደሚገኙ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከብልጽግና ፓርቲ ምክር ቤት አባላት ጋር በመሆን አዲስ የተሠራውን ከእንጦጦ እስከ አራት ኪሎ ፕላዛ የኮሪደር ሥራ መርቀዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ወቅት በሰጡት ማብራሪያ÷ የኮሪደር ልማት የኢትዮጵያን ከተሞች ገጽታ በማስዋብ ለነዋሪዎች ኑሮና የሥራ እንቅስቃሴ ምቹ ከባቢ የመፍጠር ተግባራዊ እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ በኮሪደር ልማት የተገነቡ የብስክሌት፣ የአረንጓዴ እና የመንገድ ልማት ሥራዎች መዲናዋን ውብ ገጽታ እያላበሱ መሆናቸውን የሽሮ ሜዳ፣ ካሳንቺስና ፒያሳ አካባቢዎች ማሳያ ናቸው ብለዋል።

በብልፅግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት እና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አነሳሸነትና ጥብቅ ክትትል በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች አስደናቂ የኮሪደር ልማት መከናወኑንም ተናግረዋል።

ብልጽግና ፓርቲ በከተሞች ላይ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሰው ተኮር የልማት ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ለአብነትም የመዲናዋ የኮሪደር ልማት ከዚህ ቀደም እግረኞችና አሽከርካሪዎች እየተጋፉ ሲጓዙበት የነበረውን አስቸጋሪ ሁኔታ በእጅጉ የቀየረ የልማት ሥራ መሆኑን አንስተዋል።

የመዲናዋ ነዋሪዎችም የእለት ከእለት እንቅስቃሴያቸውን በተሻለና በጥሩ ሁኔታ እንዲመሩ እያስቻለ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ምክር ቤት አባላትም ከእንጦጦ እስከ አራት ኪሎ ፕላዛ ተገንብቶ ለምርቃት በበቃው ማራኪ የኮሪደር ልማት የእግር ጉዞ ማድረጋቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ከከተሞች የኮሪደር ልማት በተጓዳኝ የገጠሩን ማህበረሰብ በሁሉም መስክ ተጠቃሚ የሚያደርግ የኮሪደር ልማት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

የከተማና ገጠር ኮሪደር ልማት ተነሳሽነት ለዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ምቹ ምኅዳር እየፈጠረ እንደሚገኝም ነው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።

ከእንጦጦ እስከ አራት ኪሎ ፕላዛ በአስደናቂ ሁኔታ የተገነባው የኮሪደር ልማት የእግረኛና ብስክሌት መንገዶች፣ የመንገድ ዳር መብራቶች፣ በታዋቂው የጥበበ ዕድ ገበያ በሽሮ ሜዳ የተገነቡ ዘመናዊ ሱቆችን አካቷል።

የኮሪደር ልማት ሥራውም የሕፃናት መጫወቻዎች፣ ሰፊ የእግር ኳስ ሜዳና ለሕዝብ አገልግሎት የሚውሉ የተለያዩ ግንባታዎች ተካተውበታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review