የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ከጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጋር በመተባበር ነፃ የበጎ ፍቃድ የጤና ምርመራ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታውቋል።
የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር እሸቱ ለማ በአገልግሎቱ 180 የጤና ባለሙያዎች ለ5 ሺህ የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች ነፃ የጤና ምርመራና ህክምና አገልግሎት እንደሚሰጡ ጠቁመዋል።
የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አብዱረዛቅ አህመድ፣ የጤና ህክምና አገልግሎቱ ከመጀመሪያ ህክምና ጀምሮ በየደረጃው የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመዋል።
ማህበረሰቡ ያለምንም ክፍያ በተዘጋጀው አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆንም ጥሪ አቅርበዋል።
ህክምና በበጎነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር አብዱረዛቅ፣ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በክረምቱ የሚያከናውነውን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህብረተሰብ ተሳትፎ እና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ አስራት ንጉሴ፣ በከተማ ደረጃ በርካታ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች እየተካሄዱ መሆኑን ተናግረዋል።
“በጎነት ለህብረተሰብ ለውጥ” በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ የሚገኘው የዘንድሮው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማካተት ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።
የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ስራ እና ክህሎት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ካሳዬ፣ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሚሰጡ 15 ዋና ዋና ተግባሮች ውስጥ አንዱ በሆነው የህክምና አገልግሎት፣ ክፍለ ከተማው ከ13 ሺህ 500 በላይ ነጻ ህክምና ለመስጠት አቅዶ ወደ ስራ መግባቱን ተናግረዋል።
አገልግሎቱ ከዛሬ ሐምሌ 28 እስከ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ለሦስት ተከታታይ ቀናት በክፍለ ከተማው ግቢ እንደሚካሄድ ተመላክቷል።
በሃብታሙ ሙለታ