አዲስ አበባ ውበትና ዘመናዊነትን ተላብሳ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቷን ከፍ ለማድረግ 24/7 በመስራት ቃል በተግባር ከተረጋገጠባቸው የማህበራዊ የልማት ሰራዎች ውስጥ የኮሪደር ልማቱ ተጠቃሽ ነው።
ይህ ስራ በተጨባጭ ከታየባቸው አከባቢዎች ውስጥ አራት ኪሎ ህያው ምስክር መሆን ችሏል።
አዲስ በተገለጠው አራት ኪሎ አከባቢ ሲገለገሉ ያገኘናቸው አቶ ፈይሳ ረጋሳ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ፣ በኔ ዘመን ግንባታዎች ተጠናቀው በአጭር ጊዜ ውስጥ ከተማዋ በዚህ ደረጃ ትዘምናለች፣ ትቀየራለችም ብዬ ጠብቄ አላውቅም ሲሉ አስተያየታቸውን ለኤ ኤም ኤን አጋርተዋል።
ለእይታ ማራኪ ያልነበረው የቀድሞው ተሻጋሪ ድልድይ መቀየር ብሎም የጋዜጣ ንባብ ስፍራው በዘመናዊ መልኩ መገለጥ የአራት ኪሎን አስደናቂ ለውጥ የሚያመላክት መሆኑን በንፅፅር አስረድተዋል።

የምሽቱ ድባብ ሌላኛው የአከባቢው ውበት የጎላበት መሆኑን የሚናገሩት ሌላኛዋ የመዲናዋ ነዋሪ ደግሞ ወ/ሮ ገነት አስፋው ናቸው።
የቀድሞ ተሻጋሪ ድልድይ ለነብሰ ጡር፣ ለህፃናት እና አቅመ ደካሞቾ የማይመች ብሎም የንፅህና ችግር የነበረበት መሆኑን ወደኋላ መለስ ብለው ያስተዋውሳሉ።
አሁን ላይ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ባማከለ መልኩ የውስጥ ለውስጥ መሻገሪያ፣ አሳንሰር ጨምሮ የማረፊያ ስፍራ አካቶ መገንባቱ አራት ኪሎን ሌላ መልክና ውበት አጎናፅፏታል ይላሉ።
ታሪክ በታሪክነቱ የሚዘልቀው ከወቅቱና ከግዜው ጋር አምሮ ዘመኑን ሲዋጅ ነው የሚሉት አቶ ፈይሳ፣ በስራው የድል ሀውልት መዋቡ በእርጅና የደበዘዘውን የታሪካዊ ቅርሶች መልዕክት ትርጉም እንዲኖረውና ተተኪው ትውልድ እንዲረዳውም ያስቻለ ነው ብለዋል።
መንግስት ለከተማ ውበትና እድገት የሠጠው ትኩረት የዜጎችን ተጠቃሚነት ከማረጋገጡም በላይ ከተማዋን ከቀድሞ ታሪኮቿ ጋር በማስተሳሰር ወደ ከፍታ እየወሰደ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።
ስራውን ማድነቅ ብቻም ሳይሆን፣ ዘመን ተሻጋሪ እንዲሆን ነዋሪው በባለቤትነት መጠበቅና መንከባከብ እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።
በሚካኤል ህሩይ