በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎችና ባለሙያዎች ማፍራቱን የፌደራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ገለጸ።
ኢንስቲትዩቱ የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም እና የተያዘው በጀት ዓመት አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ የግምገማ መድረክ በድሬዳዋ እያከናወነ ይገኛል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር(ዶ/ር)፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የሀገርን የብልጽግና ጉዞ ማሳካት የሚያስችሉ ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ስራዎችንና በክህሎታቸው የበቁ ባለሙያዎችን ማፍራት ተችሏል።
በተጨማሪም በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ በማኑፋክቸሪንግ እና በአመራር የትምህርት ዘርፎች የሶስተኛ ዲግሪ ስልጠና መርሐ-ግበር መጀመሩን ተናግረዋል።
መንግስት ለቴክኒክና ሙያ ዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠቱ ክህሎት መር ስልጠናና ዕውቀት ያላቸው ባለሙያዎች በጥራትና በብዛት ማፍራት አስችሏል ነው ያሉት።
በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ 1 ሺህ 800 የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት ከ3.5 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ክህሎት መር አጫጭርና መደበኛ ስልጠናዎችን በመስጠት ፀጋዎችን ወደ ሃብት እንዲቀየሩ በትኩረት መሰራቱን አንስተዋል።
በግምገማው ላይ የተሳተፉት የድሬዳዋ አስተዳደር የስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ሮቤል ጌታቸው በበኩላቸው፣ ኢንስቲትዩቱ ለቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችና ተቋማት ብቁና ውጤታማ አሰልጣኞችንና አመራሮች እያፈራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ለሁለት ቀናት የሚካሄደው ግምገማ የተገኙ ውጤቶችን ይበልጥ ለማስቀጠልና የታዩ ክፍተቶችን በማረም ጥራትና ተደራሽነቱ የተረጋገጠ ውጤት ለማስመዝብ እንደሚያግዝ በመድረኩ ተገልጿል፡፡
በግምገማ መድረኩ ከሁሉም ክልሎች እና ሁለቱ ከተማ መስተዳድሮች የተውጣጡ የዘርፉ አመራሮች ተሳታፊ ናቸው።