የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በየመን በደረሰው የጀልባ መስጠም በኢትዮጵያዊያን ዜጎች ላይ በደረሰው የሞት አደጋ የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገልጿል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንደገለጸው፣ የደረሰውን አደጋ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እያጣራ መሆኑን ገልጾ፣ ለሟች ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝቷል።
መንግሥት ዜጎች በተለያዩ አገራት በሕጋዊ መንገድ ተንቀሳቅሰው መሥራት እንዲችሉ ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶችን በማከናወን በርካታ ዜጎችን የዕድሉ ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑም አስታውቋል።
በዚሁ አጋጣሚ ዜጎች በሕጋዊ መንገድ ብቻ የውጭ አገራት የሥራ ሥምሪት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እና ከሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ራሳቸውን እንዲጠብቁ ማሳሰቡን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡