የአዲስ አበባ ከተማ የደንብ በማስከበር ባለስልጣን ስራቸውን በመወጣት ላይ በነበሩ የባለስልጣኑ አባላት ላይ የድብደባ ወንጀል የፈጸሙ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እየተካሄደ መሆኑ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ለኤ ኤም ኤን በላከው መረጃ ገልጿል።
ተጠርጣሪዎቹ የወንጀል ድርጊቱን የፈጸሙት ሐምሌ 26 ቀን 2017 ዓ/ም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ወረዳ 13 ልዩ ቦታው ጀሞ መስታወት ፋብሪካ አካባቢ ሲሆን ተከሳሾች ዮሀንስ ከበደ፣ ሠዒድ ሠይፉ፣ እስማኤል ሱልጣን፣ ሃይረዲን ሽፋ፣ ፈጅሩ ሱልጣን፣ ባህሩ ራህመቶ፣ ሚነወር ሀይሉ፣ ሀይልዬ ጀማልና አስማረ አለሙ የተባሉ እና ሌሎች ያልተያዙ ሁለት ተጠርጣሪዎች መኖራቸው ተጠቁሟል።
ተጠርጣሪዎቹ በእግረኛ መንገድ ላይ ህገ ወጥ የጎዳና ላይ ንግድ በማከናወን ላይ እያሉ የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን አባላት የሆኑት ማቱሳላ ማዶሬና አቡሽ ሽጉጤ ድርጊቱን ለመከላከል ሙከራ በሚያደርጉበት ወቅት ተጠርጣሪዎቹ አባሪ ተባባሪ በመሆን አባላቱን በድንጋይና በእርግጫ ተረባርበው የድብደባ ወንጀል መፈጸማቸውን ፖሊስ አስታውቋል።
ተጠርጣሪዎቹ በወቅቱ ድርጊቱን ፈጽመው ቢሰወሩም በክ/ከተማው ፖሊስ በተደረገ ክትትል በቁጥጥር ስር ሊውሉ መቻላቸውን ፖሊስ ገልጾ በፈጸሙት የወንጀል ድርጊትም ተገቢውን ምርመራ የማጣራትና ያልተያዙ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ጥረቱን መቀጠሉንም ገልጿል።
በጎዳና ላይ የሚደረጉ ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎች የእግረኛና የተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ በማወክ ዜጎችን ለመንገድ ትራፊክ አደጋ ተጋላጭ ከማድረጉም ባሻገር ጤናማ የንግድ እንቅስቃሴን የሚጎዳ መሆኑ እየታወቀ ይህንንም ድርጊት ለመከላከል የተሠማሩ የጸጥታ አካላት ላይ ትንኮሳ መፈጸምና ለህግ ተገዢ ያለመሆን ተጠያቂነትን የሚያስከትል ድርጊት መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አሳስቧል።