ክለባቸውን ትርፋማ ያደረጉ ተጫዋቾች ዝውውር

You are currently viewing ክለባቸውን ትርፋማ ያደረጉ ተጫዋቾች ዝውውር

AMN – ሐምሌ 29/2017 ዓ.ም

በአውሮፓ ለእግርኳስ ተጫዋቾች ዝውውር የሚወጣው ገንዘብ በየጊዜው እየጨመረ ይገኛል። ታላላቅ የሚባሉ የአውሮፓ ክለቦች የዝውውር መስኮት በተከፈተ ቅፅበት በሚሊየን የሚቆጠር ረብጣ ዶላራቸውን ያዘጋጃሉ።

ምርጥ የተባሉ ተጫዋቾችን ለማስፈረም ፉክክሩን ይቀላቀላሉ ። በዚህ ጊዜ የተጫዋቾቹ የመዘዋወሪያ ገንዘብ ይንራል። በርካታ ክለቦችም ትርፋማ ይሆናሉ ። በሽያጫቸው ክለቦቻቸውን ትርፋማ ያደረጉ ክለቦች በርካታ ናቸው፡፡ ለፅሁፋችን አምስት ተጫዋቾችን መርጠናል፡፡

በተከፈለበት የዝውውር ገንዘብ ክለቡን ትርፋማ ማድረግ የቻለው ቀዳሚ ተጫዋች ብራዚላዊው ኔይማር ነው ። እኤአ 2017 ክረምት የተጫዋቾች ዝውውር መስኮት ምህዳርን የሚቀይር ዝውውር ተፈፀመ።

የፈረንሳዩ ክለብ ፓሪሰን ዠርመ ኔይማር ላይ አይኑን ጣለ። ከብራዚሉ ክለብ ሳንቶስ በ88 ሚሊየን ዩሮ ያስፈረሙት ባርሰሎናዎች ተጫዋቹን የመሸጥ ፍላጎት እንደሌላቸው ገለፁ።

የፒ ኤስ ጂ ኳታራዊያን ባለሀብቶች አርፈው የሚቀመጡ አልሆኑም። የውል ማፍረሻውን 222 ሚሊየን ዩሮ ለመክፈል ተዘጋጁ። በተሰማው መረጃ የስፖርት ቤተሰቡ ጉድ አለ። ኳታራዊያኑ ግን ግድ አልነበራቸውም።

ከሊዮኔል ሜሲ ጥላ ስር ወጥቶ እራሱን ኮከብ የማድረግ ፍላጎት ያሳየው ኔይማር ለዝውውሩ ይሁንታውን ሰጥቶ ፓሪስ ደረሰ።

ባርሳም የመሸጥ ፍላጎት ባይኖረውም 134 ሚሊየን ዩሮ አተረፈ። የካታሎኑ ክለብ ከኔይማር በኋላ ተጫዋች ሲያስፈርምም ሆነ ውል ሲያድስ ውል ማፍረሻውን በቢሊየን ዮሮ ማድረግ ጀመረ።

ፍሊፕ ኩቲንሆ ከሊቨርፑል ወደ ባርሴሎና ሲያቀና የመርሲሳይዱን ክለብ በትርፍ አንበሻብሾ ነበር። በርግጥ ሊቨርፑል የመሸጥ ፍላጎት አልነበራቸውም።

ኔይማርን ባልጠበቁት መንገድ ያጡት ባርሳዎች ያቀረቡት የዝውውር ገንዘብ ላስብበት እንኳን የሚያስብል አልነበረም። ቀዮቹ ኩቲንሆን ከኢንተር ሚላን ያስፈረሙት በ13 ሚሊየን ዩሮ ሲሆን ባርሳ ደግሞ የመጨረሻ የዝውውር ገንዘብ አድርጎ ያቀረበው 135 ሚሊየን ዩሮ ነበር።

የስድስት ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒዮኑ ሊቨርፑል 122 ሚ.ዩ አትርፈው ኩቲንሆን በመሸኘት ቨርጅል ቫንዳይክ እና ግብጠባቂውን አሊሰን ቤከርን በማስፈረም የበለጠ ጠንካራ ቡድን መገንባት ቻሉ።

የኔይማር ዳ ሲልቫ ዝውውር አቅላቸውን ያሳታቸው ባርሰሎናዎች ሌላ ትኩረት ያገኘ ዝውውር ፈፀሙ ። 2017 ላይ ከቦሩሲያ ዶርትመንድ ፈረንሳዊውን ኡስማን ዴምቤሌን በ140 ሚሊየን ዩሮ አስፈረሙ።

ዴምቤሌ ከሀገሩ ክለብ ስታደ ሬኔ ዶርትመንድን ተቀላቅሎ አንድ የውድድር አመት ብቻ አሳልፎ ወደ ስፔን አቀና። ቢጫ እና ጥቁር ለባሾቹ ዴምቤሌን ያስፈረሙት በ15 ሚሊየን ዩሮ ብቻ ነበር።

ከሬኔ ጋር በነበራቸው ስምምነት መሰረት ከሽያጩ ትርፍ 15 ሚሊየን ዩሮ ሰጥተው ቀሪ 105 ሚሊየን ዩሮ ወደ ካዝናቸው አስገብተዋል።

ከባርሰሎና አልወጣንም። ከሁዋን ላፖርታ በፊት የነበሩ የክለቡ ባለስልጣናት ዝውውር ላይ የነበራቸው ተሳትፎ ክለቡን አሁንም ድረስ ዋጋ እያስከፈለው ይገኛል።

በ2019 ከአትሌቲኮ ማድሪድ አንቷን ግሪዝማንን ለማስፈረም ያወጡት 120 ሚሊየን ዩሮ አሁንም ድረስ ደጋፊዎችን ያንገበግባል። አትሌቲኮ ማድሪድ አጥቂውን ከሪያል ሶሲዬዳድ ለማስፈረም 30 ሚሊየን ዩሮ ብቻ ነበር ወጪ ያደረገው።

ክለቡን በትርፍ ያንበሻበሸው ሌላኛው ተጫዋች ጋሬት ቤል ነው። ዌልሳዊው ድንቅ እኤአ 2013 ቶተንሀምን ለቆ ሪያል ማድሪድን ሲቀላቀል የተከፈለበት 101 ሚሊየን ዩሮ የወቅቱ የአለም ክብረወሰን ነበር።

ቶተንሀም ከሳውዛምፕተን ያስፈረመበት 14.7 ሚሊየን ዩሮ ከቀነስን የሰሜን ለንደኑ ክለብ 86.3 ሚሊየን ዩሮ አትርፏል ማለት ነው።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review