ተፈጥሮ ለሠው ልጅ የተፈጠረ ልዩ ጸጋ ነው፤ የሠው ልብሱም ጉርሱም ከተፈጥሮ ነው፤ ተፈጥሮ የዕውቀት፣ የኪነት፣ የጥበብም መነሻ ነው፡፡
ይህንን ውድ እና ውብ ጸጋ የሠው ልጅ በጋራ የሚጠቀምበት ቢሆንም፣ ስለ ጸጋው በአግባቡ ተረድቶ በእንክብካቤ፣ በአድናቆት እና በምስጋና የሚጠቀሙበት ጥቂቶች ናቸው፡፡
ጥቂት ተብለው ከሚጠቀሱት የተፈጥሮን ውለታ ያልዘነጉ ሠዎች መካከል አቶ ቅዱስ ማርቆስ አንዱ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡
ትውልድ እና እድገታቸው በአዲስ አበባ ከተማ ሲሆን፣ ለተፈጥሮ እና ለስነ-ጥበብ ያላቸው ፍቅር የተለየ ነው፡፡
ተፈጥሮ ለሠው ልጅ የተሠጠ፣ ያልተቋረጠ እንክብካቤ እና ጥበቃ የሚሻ፣ ግብረ-መልሱ በሠው ልጅ አያያዝ የሚወሰን የመሆኑን ምስጢር ቀድሞ ነበር የገባቸው፡፡
አቶ ቅዱስ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ለተለያዩ ጥቅም የሚውሉ ችግኞችን በመትከል አካባቢያቸውን ውብ እና አረንጓዴ ማድረግ ችለዋል፡፡
አቶ ቅዱስ ባለፉት 9 ዓመታት ከዚህ በፊት ተራቁቶ የነበረ 900 ካሬ መሬት ላይ ቁጥራቸውን በውል መግልጽ የማይቻል ለተለያዩ አገልግሎት ሊውሉ የሚችሉ ችግኞችን መትከላቸውን ነው ከኤ. ኤም. ኤን ዲጂታል ጋር በነበራቸው ቆይታ የገለጹት፡፡
እነዚህ ችግኞች፤ አንዳዶቹ ለጥላ፣ ገሚሶቹ ለውበት እንዲሁም ሌሎች ደግሞ ለምግብነት የሚውሉ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
ሠው የቱንም ያክል በተፈጥሮ ላይ ቢያምጽም፣ ተፈጥሮ በሠው ልጅ ላይ ቂም አትይዝም፡፡ ጥፋቱን አምኖ ከአካባቢው ጋር ለሚታረቅ ማህበረሰብ የተፈጥሮ ምላሽ ፈጣንና ቸር ነው፡፡
ይህንን በአግባቡ የተረዱት የተፈጥሮ ወዳጅ አቶ ቅዱስ፣ መረዳታቸውን በተግባር የሚገልጹበትን እና ለአካባቢው ማህበረሰብ ምሳሌ የሚሆን ተግባር ለማከናወን ዓይናቸውን በመዲናዋ ከሚገኝ አንድ ሥፍራ ላይ አደረጉ፡፡
ይህ ሥፍራ በጉለሌ ክፍለ ከተማ፣ በሸጎሌ ቀለበት መንገድ ከጉለሌ ዕጽዋት ማዕከል ወደ አዲሱ ገበያ በሚወስደው መንገድ አካባቢ ይገኛል፡፡
አቶ ቅዱስ የአረንጓዴ ልማት ስራ የጀመሩት ቀደም ሲል በአካባቢ ያለው ማህበረሰብ ለቆሻሻ መጣያነት ይጠቀምበት የነበረ ስፍራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ ቦታውን ለማልማት ከመንግስት ውል ፈርመው በተረከቡት መሬት ላይ ለብዙዎች ተምሳሌት የሚሆን የአረንጓዴ ልማት ሥራ ለመከወን ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸውንና ጉልበታውን አፍስሰዋል፡፡
ከዘጠኝ ዓመታት በፊት ጀምረው ባስቀጠሉት የዕጽዋት ልማት ሥራ፤ አካባቢውን በሃገር በቀል እና የባህር ማዶ ዝርያ ባላቸው ዛፎች የተሸፈነ ጫካ ማድረግ ችለዋል፡፡
የአረንጓዴ ልማት ሥፍራውን ካለበሱት የዛፍ ዝርያዎች መካከል፤ ዋንዛ፣ ቀረሮ፣ ዝግባ፣ ግራር፣ ጃካራንዳ (አበባ ያለው የጥላ ዛፍ) እና ሌሎች ለጥላና ለውበት የሚያገለግሉ እና እያገለገሉ ያሉ የዕጽዋት ዝርያዎች ይጠቀሳሉ፡፡
አቶ ቅዱስ ባለችው መሬት ላይ የተተከሉ ችግኞች በተለያዩ ምክንያቶች ካልጸደቁ በቀጣይ በቦታቸው ሌላ ችግኝ በመትከል የመተካት ስራ እንደምሰሩ ተናግረዋል፡፡
አቶ ቅዱስ ይህንን የነፍስ ጥሪያቸውን እውን ለማድረግ በተሰጣቸው ቦታ ላይ ከመትከል አልፎ በየቤተክርስቲያኑም በርካታ ችግኞችን መትከል መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡
ይህንን በማድረጋቸው ከፍተኛ ደስታ እንደሚሰማቸውም አቶ ቅዱስ ይናገራሉ፡፡
ዕጽዋት መትከል የዕድሜ ልክ ማስታወሻ መሆኑን የተረዱት አቶ ቅዱስ፣ በዚህ ስራቸው ሌሎች በሚያወቋቸውና የስራ ባልደረቦቻቸው ዘንድ እንደ ጥሩ ተሞክሮ የሚታይ መሆኑ ይበልጥ እንዲሰሩ እንደሚያነሳሳቸው ተናግረዋል፡፡
ወደፊትም በሀገር በቀል ዛፎች የተሞላ ደን እንዲኖራቸው የሚመኙት አቶ ቅዱስ በቀጣይም ሁኔታዎች በፈቀዱ መጠን በዚህ ስራ እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡
ቢቻል ሁሉም ዜጋ ችግኝ መትከል ባህል ማድረግ መልካም ነው ያሉት አቶ ቅዱስ፣ መትከል ካልቻለ ግን ሌሎች የተተከሉትን በአቅሙ መንከባከብ፤ መንከባከብ ካልቻለ ደግሞ ባይቆርጥ የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በቶለሳ መብራቴ