በዓለም እየተስተዋለ ያለው የአየር ንብረት ለውጥ በእሲያ ሀገራትም የተለያየ መልክ ያለውን የአየር ሁኔታ ፈጥሯል።
እሲያ በዚህ በኩል በከባድ ሙቀት፤ በሌላ በኩል ደግሞ በከባድ ዝናብ እየተፈተነች ነው።
በጃፓን ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በአንድ ቀን 2 ከፍተኛ የሙቀት ደረጃዎች የተመዘገቡ ሲሆን፣ ከፍተኛው የሙቀት መጠን 41.8 ዲግሪ ሴልሺየስ ሆኖ ተመዝግቧል።
በዚህም በአብዛኛዎቹ ግዛቶቿ በሚኖሩ ሰዎች ላይ በከፍተኛ ሙቀት ምክንያት የሚከሰት ስትሮክ እንዳያጋጥም ተሰግቷል።
ጎረቤቷ ደቡብ ኮሪያም እንዲሁ እጅግ ሞቃታማ ሐምሌን ስታሳልፍ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን አልጀዚራ ዘግቧል።
በሌላ በኩል ሆንግ ኮንግ እና ደቡብ ቻይና በዚሁ የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ከባድ የተባለ ዝናብ እያስተናገዱ ይገኛል።
በደቡብ ኮሪያ በሰዓታት በዘነበ ዝናብ ሆስፒታሎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ፍርድ ቤቶች እና ሌሎችም በጎርፍ የተጥለቀለቁ ሲሆን፣ የከባድ አውሎ ነፋስ ማስጠንቀቂያም እየተሰጠ ይገኛል።
ባሳለፈው ሳምንት መጨረሻ በደቡብ ቻይና የጣለው አውሎ ነፋስ የቀላቀለ ከባድ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ፣ በጓንግዶንግ ግዛት 5 ሰዎችን ለህልፈት የዳረገ ሲሆን፣ ከ1 ሺህ 300 በላይ የነፍስ አድን ሰራተኞችም በፍለጋ ስራ እንዲጠመዱ ምክንያት መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።
በሊያት ካሳሁን