በ2017 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ አየር መንገድ 7 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱ ተገለፀ። ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ2017 በጀት ዓመት አፈፃፀምን በተመለከተ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በጀት ዓመቱ የስኬትና እቅዶች የተሳኩበት ዓመት እንደነበር ገልጿል።
አየር መንገዱ በተለያዩ የዓለም ክፍል ያሉ ግጭትና ጦርነቶች፣ የኢኮኖሚ መለዋወጥና የአሜሪካ መንግስት በተለያዩ ምርቶች ላይ የጣለውን ቀረጥ ጫና በመቋቋም የተሻለ አፈፃፀም ያስመዘገበበት እንደነበር የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው ተናግረዋል።
አየር መንገዱ በ2017 ዓ.ም በዓለም አቀፍ ዙሪያ 6 አዳዲስ ጣቢያዎችን ከመክፈቱ ባሻገር፤ 13 አውሮፕላኖችን ወደ ስራ ማስገባቱን አቶ መስፍን ጠቅሰዋል።
በዚህም በዓመቱ 15 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዓለም አቀፍ፤ 3 ነጥብ 9 ሚሊዮን የሀገር ውስጥ፤ በአጠቃላይ 19 ሚሊዮን መንገደኞችን ማጓጓዝ መቻሉን ዋና ስራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።
ዋና ስራ አስፈፃሚው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አገልግሎቱን የበለጠ ለማዘመንና ለማስፋት የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን በመስራት የደንበኞችን አገልግሎት በዲጅታል መንገድ ለማከናወን የተሰራበት ዓመት ነበር ብለዋል።
አየር መንገዱ የቱሪዝም ዘርፉን ለማስፋት መንገደኞች በኢትዮጵያ ጥሩ ቆይታ እንዲኖራቸው ሆቴሎችና ሪዞርቶችን በማቋቋም ቱሪዝሙን እያሳደገ ስለመሆኑ ተነግሯል።
በቀጣይ ዓመትም በሀገር ውስጥ ያቤሎ፣ መቱ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ሚዛን አማንና ነገሌ ቦረና እንዲሁም ሌሎች ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች በረራ ለመጀመር በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፈው 2017 በጀት ዓመት ባከናወናቸው ተግባራት በርካታ ዓለም አቀፍ ሽልማቶች ማግኘቱ ይታወሳል።
በንጉሱ በቃሉ