የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የስራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ጄንስ ሃኔፌልድን እና የግብፅ አምባሳደር ሞሀመድ ኦማር ጋድን አሰናበቱ።
ፕሬዚዳንት ታዬ አምባሳደሮቹ በነበራቸው ቆይታ አገሮቹ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ እየጎለበተ እንዲመጣ ላደረጉት አስተዋፅኦ አመስግነዋል።
ተሰናባች አምባሳደሮቹ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ካላት ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ እና ፋይዳ አኳያ፤ የሀገሮቻቸውን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በቆይታቸው አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ ተናግረዋል።
ከተሰናባች አምባሳደሮቹ ጋር የተደረገውን ውይይት የተከታተሉት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ዘሪሁን አበበ፣ ኢትዮጵያ ከጀርመን እና ግብፅ ጋር ያላትን ታሪካዊ ግንኙነት ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆኗን አብራርተዋል።
በተለይም ደግሞ ፕሬዚዳንት ታዬ የስራ ጊዜያቸውን ካጠናቀቁት የግብጽ አምባሳደር ጋር ያደረጉትን ውይይት ያወሱት አምባሳደር ዘሪሁን፣ ፕሬዚዳንቱ አምባሳደር ጋድን ለአራት ዓመት በአዲስ አበባ ላደረጉት አገልግሎት አመስግነዋል።
የኢትዮጵያ እና የግብፅ ግንኙነት እጅግ ታሪካዊ የሚባል እና በተፈጥሮ የተሳሰረ መሆኑን አውስተው፣ ይህንን ታሳቢ ያደረገ ግንኙነት መፍጠር እንዲሁም ግንኙነቱ ከፍ እንዲል ማስቻል የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው ሲሉ አጽንኦት መስጠታቸው ተጠቁሟል።
ኢትዮጵያ እና ግብጽ በአፍሪካ አህጉር ካላቸው ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ እና ተፈጥሯዊ ትስስር አኳያ ትብብራቸውን መመዘን እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።
በተለይም ደግሞ ኢትዮጵያ ከግብጽ ጋር ያላትን ታሪካዊ ግንኙነት መሰረት በማድረግ እና አገሮቹ በዓባይ ወንዝ አማካኝነት በተፈጥሮ የተቆራኙ መሆናቸውን አጽንኦት የሰጡት ፕሬዚዳንት ታዬ፣ ይህ የተፈጥሮ ሀብት በፍትሐዊነት ጥቅም ላይ እንዲውል የኢትዮጵያ የፀና አቋም እንደሆነ ማስረዳታቸውን ገልጸዋል።
ይህንን በተመለከተ ሁለቱ አገሮች በመካከላቸው ሌላ ወገን ሳይጋብዙ ተመካክረው ማናቸውንም የልዩነት መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮችን ማቃለል ይችላሉ ሲሉ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በሌላ በኩል የጀርመን አምባሳደር ጄንስ ሃኔፌልድ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ እና ጀርመን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት 120ኛ ዓመቱን አስቆጥሯል ብለዋል።
ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ልዩ ስፍራ እንደምትሰጠው የገለጹት አምባሳደር ሃኔፌልድ፣ የሁለቱ ሀገሮች ግንኙነት በሁሉም ዘርፍ ከፍተኛ ዕምርታ እንዳሳየ አብራርተዋል።