ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ በብቃት ለማስተናገድ እና ለአየር ንብረተ ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ በመገንባት ረገድ ያላትን ተሞክሮ ለማጋራት ዝግጅት ማድረጓን የፕላንና ልማት ሚንስቴር አስታውቋል፡፡
በአፍሪካ ህብረት እና በኢትዮጵያ መንግስት ትብብር በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ከጳጉሜ 3 እስከ 5 በአዲስ አበባ የሚካሄደው ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ በማስመልከት መግለጫ ተሰጥቷል።
“ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መፍትሄዎችን ማፋጠን እና የአፍሪካን የማይበገር አረንጓዴ ልማት በገንዘብ መደገፍ” በሚል መሪ መልዕክት የሚካሄደው ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ፣ የአፍሪካን የአየር ንብረት አጀንዳ እና የዘላቂ ልማት ግቦች እንዲሁም ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ለይቶ ለማራመድ አልሟል።

ይህን ዓለም አቀፍ ጉባኤ ለማካሄድ ከወዲሁ እየተሰናዳች የምትገኘው ኢትዮጵያ ጉባኤውን በብቃት ለመከዎን እየተሰሩ ስለሚገኙ የቅድመዝግጅት ስራዎች የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስዩም መኮንንን መግለጫ ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ በመገንባት ረገድ ተጠቃሽ ሀገር ናት ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ጉባኤውን በብቃት ለማስተናገድ ሁሉን አቀፍ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ፣ በግብርናው ዘርፍ፣ በታዳሽ ትራንስፖርት ዘርፍ፣ በታዳሽ የሃይል ምንጭና በመሳሰሉት ለአየር ንብረት ለውጥ አፍሪካዊና ተፈጥሯዊ መፍትሄ በመፈለግ ረገድ የፈፀመቻቸውን ስኬቶች በኤግዚብሽን እና በውይይቶች መድረኮች ልምዷን እንደምታካፍልም አቶ ስዩም መኮንን አብራርተዋል።
በጉባኤው ከ20 ሺ እስከ 25 ሺ ሰዎች የሚሳተፉ ሲሆን የ45 የአፍሪካ ሀገራትና የሌሎችም ሀገራት መሪዎች፣ የአለማቀፍ ድርጅቶች ሊቀመናብርት፣ ዲፕሎማቶች፣ አምባሳደሮች ፣ በዘርፉ የተሰማሩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣ ሲቪል ማህበራትና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት እንደሚገኙ ተመላክቷል፡፡
ጳጉሜ 3 ዋናው ጉባኤ ከመጀመሩ በፊት ከነሀሴ 30 እስከ ጳጉሜ 2 ፣ 2017 ዓም የቅድመ ጉባኤ መድረክ እንደሚካሄድም ሚኒስትር ደኤታው በመግለጫቸው ጠቁመዋል።
በይታያል አጥናፉ