ዘንድሮ በሚከናወነው የጤና በጎ ፈቃድ አገልግሎት አምስት ሚሊየን ከፍለው መታከም የማይችሉ ዜጎችን ተደራሽ ለማድረግ ወደ ተግባር መገባቱን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።
ኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ጋር በመተባበር የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ነፃ የጤና ምርመራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር አካሂዷል።
አገልግሎቱ “በጎ ፈቃደኝነት ለጤናማ ማህበረሰብ” በሚል መሪ ሀሳብ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ የጤና ምክር፣ ምርመራና ህክምና የሚሰጥበት ነው።
መርሀ ግብሩ ላይ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባን ጨምሮ የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሙሉቀን ተስፋዬ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
በዚሁ ወቅት የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መሰጠትን የሚጠይቅ መሆኑን ጠቅሰው ፤ ባለፉት የለውጥ አመታት በርካታ የበጎ ፈቃድ ስራዎች መከናወናቸውን አስታውቀዋል።
በዚህ በጎ ፈቃድ ስራዎችም ለ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሰዎች የህክምና አገልግሎት መስጠት መቻሉን ገልፀው፤ ዘንድሮ አምስት ሚሊየን ሰዎችን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል ባለፈው አመት ለ80 ሺህ አቅመ ደካሞች ነጻ የጤና ምክርና ምርመራ እንዲሁም ህክምና የተሰጠ ሲሆን ዘንድሮ 100 ሺህ ሰዎችን ተደራሽ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።
በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ ነፃ የህክምና አገልግሎት ተላላፊ የሆኑ በሽታዎችን መከላከል ላይ በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
እንዲሁም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በተመለከተ ምርመራ በማድረግ የመለየትና የቅድመ መከላከል ስራዎች ይከናወናሉ ብለዋል።
የበጎ ፈቃድ ስራ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ገልፀው፤ ይህም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ማስገንዘባቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሙሉቀን ተስፋዬ በበኩላቸው አገልግሎቱ የጤና ባለሙያዎች በጎነትን በተግባር የሚፈፅሙበት ነው ብለዋል።