በመንግስት ተቋማት ከግዥ ጋር በተያያዘ የሚስተዋለውን ሙስና እና ብልሹ አሰራር ለማስተካከል የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ስርዓትን ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ መንግስቱ አጥናፉ፣ ከኤፍ ኤም 96.3 ራዲዮ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ስርዓት የመንግሥት ተቋማት የግዥ ፍላጎታቸውን በቀላሉ የሚጠይቁበት አሰራር ስለመሆኑ ተናግረዋል።
የግዥ ስርዓቱ በመጀመሪያው ምዕራፍ በከተማዋ ዋና መስሪያ ቤቱን ጨምሮ 13 የመንግስት ተቋማት ላይ ተግባራዊ መደረጉን ጠቁመው፣ አቅራቢዎችም ምርትና አገልግሎታቸውን ያለ ውጣ ውረድ ተወዳድረው መሸጥ የሚያስችላቸው አሰራር መሆኑን አስረድተዋል።
ይህንን የግዥ ስርዓት ተግባዊ ያደረጉ ተቋማት፣ አሁን ላይ ውስን ጨረታን ተጠቅመው ግዥ እያከናወኑ ስለመሆኑ አንስተው፣ በቀጣይም በግልጽ ጨረታ የማዕቀፍ ግዥዎችን ወደ ስርዓቱ ለማስገባት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የጨረታ ሂደት አሰልቺ እና ለብልሹ አሰራር የተጋለጠ እንደነበር ዋና ስራ አስኪያጁ አስታውሰው፣ የመንግሥት የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ስርዓት ይህን በማስተካከል የመንግሥትና ህዝብን ሃብት ከብክነት የሚታደግ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በተያዘው በ2018 በጀት አመትም ሌሎች የመንግሥት ተቋማት ወደ ኤሌክትሮኒክ ግዥ ስርዓት እንዲቀላቀሉ ለማድረግ በትኩረት እየተሰሩ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡
በሽታሁን መንግስቴ