ወንዞች ሲታከሙ …………

You are currently viewing ወንዞች ሲታከሙ …………

“ከዚም ከዚያም መጥተን ዋኝተናል ቀበና፣
‎ፍቅር አጠራርቶን ከፈረንሳይ ቤላ፣
‎ቀበና ታደምን ከአቧሬ እስከ ሾላ፡፡
‎ምንም ብንራራቅ ቢለያይ ደብራችን፣
‎ከማዶ እስከ ማዶ አንድ ነው ወንዛችን፡፡
‎ቢሻን ቢሻን ቀበና ቢሻን ቢሻን ………….”
እነዚህ ስንኞች ከዘጠናዎቹ በፊት ለነበሩት ታዳጊዎች ከቀበና ወንዝ ጋር ያሳለፉትን ወደ ኋላ በትዝታ የሚወስድ ነው።

ወንዙ ለአከባቢው ታዳጊዎች መዋኛና መዝናኛ ከመሆኑ ባሻገር መሰባሰቢያቸው ጭምር እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ መሆኑ ይታወቃል።

ለዚያም ይመስላል ድምፃዊ ፀሃዬ ዮሃንስ በቀበና ወንዝ ከእኩዮቹ ጋር ያሳለፋቸውን እና ያደረጋቸውን ትውስታዎች ወደ ኋላ በትውስታ ዘፈኑ ወንዙን ያስቃኘን።

አዲስ አበባ ከተማ ካሏት ወንዞች ውስጥ ቀበና አንዱ ቢሆንም ለዓመታት ታዳጊዎች ሊዋኙበት ቀርቶ በአከባቢው ለማለፍም የሚከብድ አፍንጫን እሚሰነፍጥ ሽታ እንደነበረው ይታወቃል።

ከ140 ዓመታት በላይ እድሜ እንዳላት የሚነገርላት አዲስ አበባ ከተማ ለመመስረቷ ወንዞቿ እና ምንጮቿ እንደሆኑ ታሪክ ያስረዳል። የመዲናዋ ሃብት እና ፀጋ የነበሩ ወንዞች ለነዋሪዎቹ የጤና ጠንቅ እና የጎርፍ እደጋ መንስኤ ሆነው ዘልቀዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አካታች የመሰረተ ልማት ተጠቃሚነትን ተደራሽ ለማድረግ ከሚከናወኑ ስራዎች መካከል ለኮሪደር ልማቱ አንድ አካል የሆነው የወንዞች እና የወንዞች ዳርቻ ልማትን ያካትታል ።

ይህ ፕሮጀክት አዲስ አበባ ከተማን እንደ ስሟ አዲስ እና ውበ ከማድረግ በተጨማቀሪ ለነዋሪዎች ምቹ ለማድለግ ያለመ መሆኑ ይታወቃል ።

የእነዚህ ፕሮጀክት ትልም ይህ ብቻ አይደለም፤ የአፍሪካ መዲና እና የዓለም ዲፕሎማቶች መቀመጫ የሚመጥን ከተማ ከማድረግ አኳያ ሚናው ላቅ ያለ ነው።

አስራ አንድ ወራትን የተሻገረው የወንዞች እና የወንዞች ዳረቻ ልማት እየተገባደደ እንደሚገኝም ተመላክቷል፡፡

ይሁን እንጂ ምሽትንና ዝናብን ተገን አድርገው ፍሳሽ ቆሻሻን ወደ ወንዞች የሚለቁ ተቀማት እንዳሉ የእንጦጦ -ፍሬንዲሽፕ የወንዞች እና የወንዞች ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ምክትል ዋና አስተባባሪ አቶ ዋለልኝ ደሳለኝ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል ተናግረዋል።

ለአዲስ አበባ ከተማ መመስረት ምክንያት የሆኑ ወንዞችን ከብክለት ለመጠበቅ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ሀላፊነታቸውን መወጣት እዳለባቸው የገለፁት አቶ ዋለልኝ፣ ነዋሪዎችም እነዚህን ተቀማት ጥቆማ በመስጠት የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል ።

የአዲስ አበባ ወንዞች ለረጅም አመታት የደረቅ እና የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ ሆነው መቆየታቸውን የገለፁት አቶ ዋለልኝ፣ በቅርቡ የተጀመረው መዲናይቱን እንደስሟ አዲስ የማድረግ ትልም ተግባራዊ እየተደረገ ቢሆንም አንዳንድ አካላት አሁንም ወንዞችን እየበከሉ መሆኑን ጠቁመዋል።

ወንዞቹ በተለያዩ በደረቅ እና በፍሳሽ ቆሻሻ ሳቢያ ነዋሪዎች ለተላላፊ በሽታዎች ከመጋለጣቸውም በተጨማሪ ለጎረፍ አደጋ ተጋላጭ ሆነው መቆየታቸውን አስረድተዋል፡፡

ይህን ለመከላከልና ወንዞችን ለመጠበቅ ከተማ አስተዳደሩ ደንብ ቁጥር 180/ 2017 በማውጣት ወደ ስራ መግባቱን አቶ ዋለልኝ ገልጸዋል።

ይህ ህግ ተግባራዊ ቢደረግም ዝናብን፣ ምሽትንና ሰው አየኝአላየኝ ብለው ወደ ወንዞቹ ውስጥ ደረቅ እና ፍሳሽ ቆሻሻ የሚለቁ ተቋማት እንዳሉ ገልፀው፣ መንግስት እስካሁን ድርጊቱን በሚፈፅሙ አካላት ላይ እርምጃ ሲወስድ መቅየቱን አስታውሰዋል።

ይሁን እንጂ የተቀመጠውን ህግ ጥሰው አሁንም ከድርጊታቸው ያልተቆጠቡ ተቋማት እንዳሉ ገልፀው፣ ተቋማቱ ይህንን እኩይ ድርጊታቸውን ከቀጠሉ ህዝብን ያሳተፈ ጠንካራ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው በአፅንኦት ተናግረዋል።

የወንዞች እና የወንዞች ዳርቻ ፕሮጀክት በፍጥነት እየተሰራ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ዋለልኝ፣ በቅርቡ ተጠናቆው ለህዝብ ክፍት ስለሚደረግ ህብረተሰቡ ወንዞቹን ከሚበክሉ ነገሮች እንዲጠብቃቸው ጥሪ አቅርበዋል።

ፕሮጀክቱ በአምስት ክፍለ ከተሞች፣ በ12 ወረዳዎች፣ በስድስት ሴግመንት እና በአምስት ዞኖች ተከፋፍሎ በፍጥነትና በጥራት እየተከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በወንዞች አካባቢ የሚገኙ እና ውኃ የመምጠጥ አቅማችው ከፍተኛ የሆኑ ዛፎችን በማስወገድ፣ ስነ ምህዳርን የሚጠብቁ ሀገር በቀል ችግኞች እየተተኩ መሆኑንም ጠቁመዋል።

አጠቃላይ በመዲናይቱ እየተሰሩ የሚገኙት ሁለቱ ኘሮጀክቶች ርዝመት 41 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን፣ በውስጡ የውሃ ማጣሪያ፣ የንጽህና መጠበቂያ፣ የብስክሌትና የእግረኛ መንገድ፣ የኤሌክትሪክ ዝርጋታ፣ የአስፓልት መንገድ፣ 17 ዘመናዊ ድልድዮች፣ የነዳጅ ማደያ እና የተለያዩ አገልግሎቶችን ያካተተ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል።

‎በሔለን ተስፋዬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review