የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ብሄራዊ ጥቅም እና በሰላም ጉዳይ ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችል “የቢሾፍቱ ቃል ኪዳን” ስምምነት አድርገዋል።
በቢሾፍቱ ሲካሄድ የቆየው ይህ ኮንፍረንስ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ሰላም በማፅናት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና በሚል መሪ ቃል ሲያካሂድ መቆየቱ ይታወሳል።
የቃል ኪዳን ስምምነቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለአገራዊ መግባባት፣ ብሄራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ እና የሰለጠነ የፖለቲካ ስነ ምህዳር የማስፋት ይዘት ያለው ስምምነት መሆኑን ከኤ ኤም ኤን ጋር ቆይታ ያደረጉ የፖለቲካ ፖርቲዎች ተናግረዋል።
የቦሮ የዴሞክራሲ ፖርቲ ስራ አስፈፃሚ መብራቱ አለሙ ዶ/ር፣ የቃል ኪዳን ስምምነቱ የሰላም ምንነቶችና መገለጫዎች የግንዛቤ ሀሳብ የተወሰደበት እንደሆነ ተናግረዋል።
የሰነዱ መዘጋጀት ዋነኛ አላማ በተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች እንደሆኑ ጠቁመው፣ እነዚህን ችግሮች የፖለቲካ ፖርቲዎች ሚናቸውን ተወጥተው በሰላማዊ መንገድ ችግሮች እንደሚፈቱ ለማስመዝገብ እንደሆነ ስራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።
ፖለቲካ ማለት ግጭቶችን በውይይት፣ በምክክር፣ በሽምግልና መፍታት ማለት ነው ያሉት የፖርቲው ስራ አስፈፃሚ፣ በሰላሚዊ መንገድ ችግሮችን ለመቅረፍ ስምምነቱ ያግዛል ብለዋል።
የዴሞክራሲ ባህልና እሴቶች እንዲዳብሩ የቃል ኪዳን ስምምነቱ እንደሚያግዝ፣ ልዩነቶችና ችግሮችን በጠረንጴዛ ዙሪያ ለመፍታት እንደነዚህ ያሉ መድረኮች የነበረውን እሳቤ የሚቀይሩ መሆናቸውም ተገልጿ፡፡
በአገራዊ እና ብሄራዊ ጥቅም ጉዳይ የፖለቲካዊ ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው ለጋራ መሰለፍ ሌላኛው የቃልኪዳኑ ስምምነት አንኳር ጉዳይ መሆኑም ተመላክቷል።
የአዲስ ትውልድ ፖርቲ ፕሬዝዳንት አቶ ሰለሞን ታፈሰ በበኩላቸው፣ ቃልኪዳኑ እያንዳንዱ የፖርቲ አባል በሚኖርበት አከባቢ ሰላም የማስፈን አስተዋፅኦቸውን እንዲወጡ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
ከመንግስት ጋር አንድ የሚያደርጋቸውን ጉዳዮች በሶስት የከፈሉት አቶ ሰለሞን፣ የአገር ጉዳይ፣ የሰላም ጉዳይ፣ በአገሪቱ የሚሰሩ መሰረተ ልማቶች የጋራ መሆናቸውን ይገልፃሉ።
ሐምሌ 17 ቀን 2017 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ የተከናወነው የቢሾፍቱ ቃል ኪዳን ስምምነት ሰባት አንቀፆችን በውስጥ ያካተተ ስምምነት ነው።
ከእነዚህ ስምምነቶች ውስጥ ለብሄራዊ ጥቅምና ለዴሞክራሲ ስረዓት የማፅናት፣የግልፀኝነትና የተጠያቂነት መርህ የማዳበር፣ የግጭት አያያዝና የሰላም ግንባታ ውጤታማነት የመስራት፣ ለአካታችነት፣ ለአገራዊ መግባባትና ብሄራዊ ጥቅም አብሮ የመቆም የሚሉት ጉዳዮች ይገኙበታል።
በሔለን ተስፋዬ