በርካታ ታዳጊ ሀገራት የባህር በር አልባ መሆናቸው በዓለም የኢኮኖሚ ሥርዓት ላይ ፍትሐዊ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ እያደረጋቸው እንደሚገኝ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈትሂ ማህዲ(ዶ/ር) ገለጹ።
3ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የባሕር በር የሌላቸው በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት ጉባኤ በተርክመኒስታን አዋዛ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በጉባኤው እየተሳተፉ የሚገኙት ዶክተር ፈትሂ ማህዲ ለኢዜአ በሰጡት ማብራሪያ÷ ኢትዮጵያን ጨምሮ የባህር በር የሌላቸው ታዳጊ ሀገራት ጥቅምና ፍላጎታቸውን ማስከበር የሚያስችል ተሳትፎ እያደረጉ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ(ዶ/ር) የሚመራ የኢትዮጵያ ልዑክም የሀገርን ጥቅምና ፍላጎት ማስገንዘብ የሚያስችል የነቃ ተሳትፎ እያደረገ ነው ብለዋል።
ከጉባኤው በተጓዳኝ በተካሄዱ የወጣቶች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና የሕዝብ ተወካዮች የቅድመ ጉባኤ ፎረሞች ላይ የኢትዮጵያ ተወካዮች ንቁ ተሳትፎ ማድረጋቸውን አስረድተዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ቅድመ ጉባዔ የፓናል ውይይትም ’’የባሕር በር መዳረሻ የሌላቸው ታዳጊ ሀገራትን ተጠቃሚ የሚያደርግ የንግድ ሥርዓት ማቋቋምና ማጠናከር” በሚል ርዕሰ ጉዳይ ጽሁፍ ማቅረባቸውን አስታውቀዋል።
በጽሁፋቸውም ኢትዮጵያ የባሕር በር የሌላት መሆኑ በወጪና ገቢ ምርት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዋ ላይ ቀጥተኛ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን ማስገንዘብ እንደተቻለ አብራርተዋል።
በተለይም የኢትዮጵያ የወደብ ባለቤት አለመሆን የወጪና ገቢ ምርት እንቅስቃሴና የምርቶች ዋጋ ላይ ጫና እያስከተለ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም ኢትዮጵያ የባሕር በር መዳረሻ ሳይኖራት በመቆየቷ ሁለንተናዊ ዕድገቷንና ብልጽግናዋን ለማረጋገጥ በምታደርገው ጉዞ ትልቅ እንቅፋት መፍጠሩን አስረድተዋል።
የባህር በር የሌላቸው ታዳጊ ሀገራት በዓለም አቀፍ የንግድ ሥርዓት ላይም ፍትሕዊና እኩል ተጠቃሚ መሆን አለመቻላቸውን ለተሳታፊ ሀገራትና ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማስገንዘብ ተችሏል ብለዋል።
ይህም ሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገታቸውን እንዳያፋጥኑ እንዲሁም ከባህር ለሚነሱ የደህንነት ስጋቶች ተጋላጭ እንዲሆኑ እያደረገ እንደሚገኝ አንስተዋል።
በዚህም የባሕር በር የሌላቸው ታዳጊ ሀገራት ሕግ አውጪዎች ጉዳዩን ታሳቢ ያደረገ ስራ መስራት እንዳለባቸው ምክክር መደረጉን ጨምረው ተናግረዋል።
በተለይም ቀጣናዊ ትስስርን የሚፈጥሩ የወደብና የመንገድ መሠረተ ልማት ትስስሮችን የሚያሳልጥ የበጀትና ተያያዥ የድጋፍና ክትትል ስራ መስራት እንደሚገባ በመድረኩ አፅንኦት መሰጠቱን ጠቅሰዋል።
የባህር በር ያላቸው ሀገራትም ለፍትሕዊ የንግድ ስርዓት መጠናከርና የባህር በር የሌላቸው ሀገራትን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ገልጸዋል።
በኮንፍረንሱ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ፣ እስያ፣ አውሮፓ እና ደቡብ አሜሪካ የሚገኙ 32 ሀገራት እየተሳተፉ ሲሆን፤ ከተሳታፊዎቹ ሀገራት መካከልም 16ቱ ከአፍሪካ ናቸው።
ሶስተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የባህር በር የሌላቸው በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት ኮንፍረንስ እስከ ነሐሴ 2 ቀን 2017 ዓ.ም የሚቆይ ይሆናል።