ኢትዮጵያና ተርኪሚኒስታን በባህር በር ምክንያት የሚከሰቱ ተግዳሮቶችን በጋራ ለመፍታት እንዲሁም ቀጣናዊ ውህደትንና ንግድን ለማጠናከር ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።
ሦስተኛው የተባበሩት መንግሥታት ባህር በር የሌላቸው በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ጉባኤ (UNLLDC3) “በአጋርነት ለውጥ ማምጣት” በሚል መሪ ሀሳብ በተርኪሚኒስታን አስተናጋጅነት እየተካሄደ ይገኛል።
ከጉባኤው በተጓዳኝ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ከተርኪሚኒስታኑ የንግድና የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ሚኒስትር ናዛር ሃልናዛሮቪች አጋሃኖቭ ተወያይተዋል።
ሁለቱ ሀገራት ኢ-ፍትሃዊ የሆነውን የባህር በር ተግዳሮት በጋራ ለመፍታት የመከሩ ሲሆን፤ ለንግድና ኢኮኖሚ እድገት መፋጠን አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ቀልጣፋና አነስተኛ ወጪ ያላቸውን የትራንስፖርት መፍትሄዎች ለመፍጠር ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማምተዋል።
ሚኒስትሮቹ ከፍተኛ የትራንስፖርት ወጪ፣ በጎረቤት ሀገራት ወደቦች ላይ ሙሉ ጥገኝነት እና የንግድ መስመሮችን የሚያውኩ የጂኦ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ስጋቶችን ጨምሮ የተለያዩ ተግዳሮቶችን አንስተዋል።
ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) የባህር በር አለመኖር ለረጅም ጊዜ የሀገራትን ልማት የሚያደናቅፍ መልክዐ ምድራዊ ተግዳሮት መሆኑን ጠቅሰው ይህንን ተግዳሮት ወደ መልካም አጋጣሚ ለመቀየር የዚህ ዓለም አቀፍ መድረክ ታላቅ ሚና እንደሚጫወት ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።
ናዛር ሃልናዛሮቪች አጋሃኖቭ በበኩላቸው ቀጣናዊ ውህደት የባህር በር አልባ ሀገራትን እምቅ አቅም ለማውጣት ቁልፍ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
መፍትሔው ሀገራቱ በቀጣናቸው ውስጥ ያልተቋረጠ የሸቀጦች፣ የአገልግሎቶችና የሃሳቦች ፍሰት በሚፈጥር የግንኙነት መስመር መዘርጋት መሆኑን ገልጸዋል።
አክለውም ተርኪሚኒስታን ይህንን እውን ለማድረግ የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶችን ለመገንባትና አስፈላጊ ስምምነቶችን ለመፈጸም ቁርጠኛ ናት ብለዋል።
ኢትዮጵያን በዚህ ጥረት ውስጥ እንደ ዋና አጋር እንደሚመለከቱ እና ሀገራቸው የመካከለኛው እስያ መግቢያ በር እንደሆነች ሁሉ ኢትዮጵያም የአፍሪካ መግቢያ በር መሆኗን ጠቅሰዋል።
ሚኒስትሮቹ በጉባኤው ለሀገራቱ ቁልፍ መፍትሔዎች እንደሚቀርቡ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያና ተርኪሚኒስታን አጋርነታቸውን ለማስፋትና በባህላዊ የንግድ መስመሮች ላይ ያላቸውን ጥገኝነት ለመቀነስ እንዲሁም የተቀላጠፈ አሠራር ላይ የተመሠረተ አዲስ የንግድ አጋርነትን ለመመስረት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ኢዜአ ከስፍራው ኢዜአ ከስፍራው ያገኘው መረጃ ያመለክታል።