መንግስት ከገበያ ባፈነገጠ ሁኔታ የትይዩ የውጭ ምንዛሬ እንዲስፋፋ በሚሰሩ ህገ-ወጥ ድርጅቶች ላይ ጠንካራ ህጋዊ እርምጃ መውሰዱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ ገለጹ።
በህገ-ወጥ ድርጊቱ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች እንደ አስፈላጊነቱ ለህዝብ ይፋ ይደረጋሉም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ ወቅታዊ የውጭ ምንዛሪ ገበያን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
አቶ ማሞ ባንኩ በመደበኛነት እያካሄደ ያለውን የውጭ ምንዛሬ ጨረታውን ለመቀጠል መወሰኑንም ገልጸዋል።
ባለፈው ዓመት የብሔራዊ የውጭ ምንዛሬ መጠባበቂያ ክምችት በሶስት እጥፍ መጨመሩ እና ይህ መልካም ውጤት በተያዘው በጀት መቀጠሉ እንዲሁም የባንኩ የውጭ ምንዛሬ ፍሰት እና ግኝት ከተጠበቀው በላይ ማደጉ ጨረታው እንዲቀጥል ምክንያት መሆናቸውን አመልክተዋል።
ከውጭ ምንዛሬ ገቢው ከፊሉ ለባንኮች መቅረቡ ባንኮች ያላቸውን የውጭ ምንዛሬ ከማሳደግ ባሻገር ዋጋ እና የውጭ ምንዛሬ የማረጋጋት ስራን ለማሳካት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
ትናንት በተደረገው የ150 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ጨረታ 28 ባንኮች በጨረታው መሳተፋቸውን ገልጸው ሁሉም ባንኮች የሚፈልጉትን የውጭ ምንዛሬ ማግኘታቸውንና አንድ ዶላር 138 ብር መሸጡን ጠቁመዋል።
ባንኮቹ በጨረታው ያገኙትን ጨምሮ የራሳቸውን ገቢ በመጨመር በቂ የውጭ ምንዛሬ እንደሚያቀርቡ ይጠበቃልም ነው ያሉት።
የንግዱ ማህበረሰብ እና የግሉ ዘርፍ ባንኮች በሚያቀርቡትን የውጭ ምንዛሬ እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።
በሌላ በኩል አብዛኞቹ የንግድ ማህበረሰብ አባላት በመደበኛ እና ህጋዊ የውጭ ምንዛሬ ስርዓት ውስጥ የሚሳተፉ ቢሆንም አንዳንዶች በትይዩ የውጭ ምንዛሬ ገበያ ውስጥ እየተሳተፉ እንደሚገኙ ነው የባንኩ ገዥ ያመለከቱት።
በህገ ወጥ ድርጊቱ ላይ የሚሳተፉ የንግዱ ማህበረሰቦች ወደ መደበኛ ስርዓቱ እንዲመለሱ ያሳሰቡ ሲሆን ከድርጊታቸው በማይቆጠቡት ላይ ሀብታቸውን እስከ መውረስ የሚደርስ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ አስጠንቅቀዋል።
ባንኮች ከውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ጋር በተገናኘ በንግዱ ማህበረሰብ አባላት ይቀርብባቸው የነበሩ አብዛኞቹ ቅሬታዎች መፈታተቸውን የገለጹት አቶ ማሞ ቀሪ ተግዳሮቶች መፍትሄ እንዲያገኙ እየሰሩ ይገኛል ነው ያሉት።
ብሄራዊ ባንክ የኢትዮጵያን የፋይናንስ ስርዓት ተአማኒነት ሆን ብለው ለመሸርሸር እና የገበያ ዋጋ መዛባትን በማለም እየሰሩ ያሉ በውጭ የሚገኙ ህገ-ወጥ የውጭ ምንዛሬ አዘዋዋሪዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን እንደሚቀጥልም አስገንዝበዋል።
ባንኩ እንደ አስፈላጊነቱ በዚህ ህገ ወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩ ድርጅቶችን ስም ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።
ተቀማጭነታቸውን በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዱባይ ያደረጉ ከገበያ ባፈነገጠ ሁኔታ የትይዩ ገበያውን ለማስፋት በሚሰሩ ህገወጥ ድርጅቶች ላይ እርምጃ እንደሚወስድም አብራርተዋል።
አሳሳች መረጃን ከማሰራጭት ጋር በተያያዘም ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ነቀፌታ አቅርቧል የሚለው መረጃ መሰረተ ቢስ እና ከእውነት የራቀ መሆኑን ነው ያብራሩት።
አይኤምኤፍ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ያለው አጠቃላይ እይታ እጅግ አዎንታዊ ነው ያሉት አቶ ማሞ የሚያወጣቸው መረጃዎች እና ሪፐርቶች ይሄን የሚያመላክቱ ናቸው ብለዋል።
በውጭ ምንዛሬ ስርዓት እና አጠቃላይ የኢኮኖሚ ሪፎርሙ የተገኙ አዎንዊ ውጤቶች ኢትዮጵያ በትክክለኛ የእድገት ጎዳና ላይ እንደምትገኝ ያሳያሉ ነው ያሉት።
በአዲሱ በጀት መጀመሪያ ላይ የታየው አበረታች የውጭ ምንዛሬ ክምችት እድገት በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መናገራቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።
አቶ ማሞ ማህበረሰቡ ከሀሰተኛ መረጃዎች እና አሳሳች አሉባልታዎች ራሱን በመጠበቅ መደበኛ የንግድ እንቅስቃሴውን ያለ ምንም ስጋት እንዲያከናውን ጥሪ አቅርበዋል።