በቀጣይ ሁለት ወራት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ አካባቢዎች ከመደበኛ በላይ የዝናብ ስርጭት እንደሚጠበቅ ኢንስቲትዩቱ ገለጸ

You are currently viewing በቀጣይ ሁለት ወራት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ አካባቢዎች ከመደበኛ በላይ የዝናብ ስርጭት እንደሚጠበቅ ኢንስቲትዩቱ ገለጸ

AMN ነሐሴ 1/2017

በቀጣይ ሁለት ወራት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ አካባቢዎች ከመደበኛ በላይ የዝናብ ስርጭት የሚጠበቅ በሆኑ የጎርፍ ስጋት ተጋላጭነትን ለመቀነስ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ የክረምት ወቅት አጋማሽ የአየር ጸባይ ተጽዕኖ አጠቃላይ ግምገማና በቀሪው የክረምት ወራት የሚጠበቅ የአየር ጸባይ አዝማሚያ ላይ መግለጫ ሰጥቷል።

የኢንሰቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ በሰጡት መግለጫ ኢንስቲትዩቱ የበጋ፣ የበልግና የክረምት ወቅት የአየር ጸባይ ትንበያዎችን እያቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም የክረምት ወራት የዝናብ ተጠቃሚ የሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን ማሳለጥ የሚያስችል የዝናብ ስርጭት እንዳለ ገልጸዋል።

የክረምት ወቅት ዝናብ ተጠቃሚዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ የዝናብ ስርጭት እያገኙ መሆኑን ጠቅሰው ይህም የሰብል ልማትን ጨምሮ ለግብርና፣ ለግድቦች መሙላት፣ ለከርሰ ምድር የውሃ ሀብት መጨመርና ለመስኖ ልማት የሚውል በቂ ውሃ ለመያዝ ጥሩ አጋጣሚ ነው ብለዋል።

የሰኔና የሐምሌ ወር የዝናብ ስርጭት በ227 የኢንስቲትዩቱ ጣቢያዎች ላይ በከፍተኛነት የተመዘገበባቸው መሆኑንም ነው የተናገሩት።

በቀጣይ ነሐሴና መስከረም ወራትም መደበኛና ከመደበኛ በላይ የዝናብ ስርጭት የሚኖር በመሆኑ ለመኸር አብቃይ አካባቢዎች ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ሲሆን እርጥበት አጠር የሆኑ አካባቢዎችም ከፍተኛ ውሃ እንዲይዙ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በእርሻ ማሳ ላይ የውሃ መተኛት፣ ሰብሎች በውሃ የመዋጥ፣ የአፈር መሸርሸርና የመሬት መንሸራተት፣ በገጠርና በከተሞች የጎርፍ አደጋዎችን ማስከተል ስለሚችል በቅድመ ጥንቃቄ ስራ ላይ በትኩረት መሰራት ይገባል ብለዋል።

የጎርፍ ተጋላጭነትን ለመቀነስ በገጠርና በከተሞች የውሃ መውረጃ ቦዮችን ማፅዳትና ማስተካከል እንዲሁም ለመሬት መንሸራተት አደጋ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች ላይ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ መክረዋል።

ኢንስቲትዩቱ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርን ጨምሮ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የአየር ጸባይ ትንበያ መረጃን በአግባቡ ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ መግለጻቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።

በተጨማሪም አብዛኛው የክረምት ወራት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ የአዋሽ፣ አባይ፣ ባሮ አኮቦ፣ ጊቤና ሌሎች ተፋሰሶች ላይ የጎርፍ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሁሉም ሴክተሮች ቅንጅት የታከለበት ስራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review