በበጀት ዓመቱ ተቋሙ ከፍተኛ ጥራት ያላቸው የይዘት ስራዎችን ተደራሽ ያደረገበት መሆኑን የጠቀሱት ዋና ስራ አስፈፃሚው ለዚህም ከከማ አስተዳደሩም ሆነ ከሌሎች ተቋማት በተለያየ ጊዜ እውቅና ያገኘበት መሆኑን አስታውሰዋል።
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የ2017 በጀት ዓመት የስራ አፈፃፀም ግምገማ እና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ከተቋሙ አመራሮች እና አጠቃላይ ሰራተኞች ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
በመርሐ-ግብሩ የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ፣ ተቋሙን በይዘቱ ተመራጭና ቀዳሚ ሚዲያ ለማድረግ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ኤ ኤም ኤን በ2017 በጀት ዓመት የህዝብ የመልካም አስተዳደር እና የአገልግሎት አሰጣጥ ጥያቄዎች እንዲመለሱ እንዲሁም ነዋሪውን ህብረተሰብ ከአስተዳደሩ ጋር በማገናኘት ረገድ ውጤታማ ስራ በማከናወን ባሳየው ጥሩ አፈፃጸም ልዩ ተሸላሚ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ዕውቅናው የምንዘናጋበት ሳይሆን በቀጣይ የበለጠ እንድንሰራ የተሰጠን ትልቅ የቤት ሥራ ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው፣ በ2018 በጀት ዓመት በቅንጅት ሰርተን የተጣለብንን ኃላፊነት እንወጣለን በማለት ገልጸዋል፡፡
ወቅታዊና ሀገራዊ እንዲሁም ህብረተሰቡ የሚፈልገውን አጀንዳ ቀድሞ በመረዳት በ2018 በጀት ዓመት የተሸለ ስኬት ለማስመዝገብ እርብርብ እንደሚደረግም ተናግረዋል።
ለሰራተኛው ምቹ ሁኔታን በመፍጠር እና ቴክኖሎጂን በመጠቀም፣ ይዘቶችን ከፍ በማድረግ ተወዳዳሪ የሚያደርጉ ሥራዎችን ለመስራትም በቁርጠኝነት መነሳት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በታምራት ቢሻው