የኢትዮጵያ እና የቻይና ወዳጅነት ዘርፈ ብዙ፣ ታሪካዊና ውጤታማ ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታየ አፅቀስላሴ ገለፁ።
የቻይና በጎ ፍቃደኛ የጤና ባለሙያዎች፣ የአፍሪካ በጎ አድራጊ ቡድኖችና ዓለም አቀፍ በጎ ፍቃደኛ የጤና ባለሙያዎች በትብብር ነፃ የጤና ህክምና ማድረግ ጀምረዋል።
በበጎ ፈቃድ ማስጀመሪያ መርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታየ አፅቀስላሴ፣ የኢትዮጵያ እና የቻይና ወዳጅነት በቴክኖሎጂና በሳይንስ ብቻ ሳይሆን በባህልና በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የተቃኘ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል።

የቻይና በጎ ፈቃደኛ ዶክተሮች ለበጎ ፍቃድ አገልግሎት ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት ለማጠናከር ቁልፍ ተግባር መሆኑንም ተናግረዋል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው፣ በጤናው ዘርፍ በኢትዮጵያ እና በቻይና መካከል ያለው ትብብር ምሳሌ የሚሆንና ሊበረታታ የሚገባ መሆኑን ገልፀዋል።
የበጎ ፍቃደኛ የጤና ባለሙያዎቹ የጤና በጎ ፍቃድ አገልግሎት ለመስጠት መምጣታቸው በጤናው ዘርፍ ለመስጠት የታቀደውን የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚያግዝ ነው ብለዋል።
በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ችን ሄይ የቻይና- አፍሪካና የቻይና-ኢትዮጵያ ወዳጅነትን በጤናው ዘርፍ አጠናክሮ ለማስቀጠል ቻይና ቁርጠኛ መሆኗን ገልፀዋል።
በጎ ፍቃደኞች ከ40 በላይ የሚደርሱ ሲሆኑ፣ በአይን፣ በአዕምሮ፣ በልብ ቀዶ ህክምና እና በማህፀን ምርመራ ህክምና እንደሚሰጥ ተነግሯል።
የበጎ ፍቃድ የጤና አገልግሎቱ በአዲስ አበባ ሲልክ ሮድ አጠቃላይ ሆስፒታል የሚሰጥ ሲሆን፣ ሁለት ሳምንት እንደሚቆይ ተመላክቷል።
በንጉሱ በቃሉ