የእስራኤል የጸጥታ ካቢኔ የጋዛ ከተማን ለመቆጣጠር የቀረበውን እቅድ አጸደቀ

You are currently viewing የእስራኤል የጸጥታ ካቢኔ የጋዛ ከተማን ለመቆጣጠር የቀረበውን እቅድ አጸደቀ

AMN- ነሐሴ 2/2017 ዓ.ም

የእስራኤል የጸጥታ ካቢኔ ጋዛ ከተማን ለመቆጣጠር የሚያስችል እቅድ ማፅደቁን የጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ከካቢኔው ስብሰባ ቀደም ብለው የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ጋዛን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረው ነበር።

አሁን በካቢኔ የጸደቀው እቅድ በተለይ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በሚኖሩባት በጋዛ ከተማ ላይ ማተኮሩ ታውቋል።

እስራኤል ጋዛን ለመቆጣጠር የያዘችወ ዕቅድ መፅደቁን ተከትሎ የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ኬይር ስታርመር፣ እስራኤል በጋዛ ላይ የምታደርሰውን ጥቃት ማባባሷ ስህተት እና ተጨማሪ ደም መፋሰስን ያመጣል ሲሉ ኮንነዋል።

ኬይር ስታርመር የእስራኤል መንግስት ጋዛን ለመቆጣጠር ያፀደቀውን እቅድ ካቢኔው በአስቸኳይ እንዲያጤነውም አሳስበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ይህ እርምጃ ፣ ግጭቱን ለማስቆምም ሆነ ታጋቾችን ለማስለቀቅ የሚረዳ ምንም ነገር አይኖርም ብለዋል።

የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ለግጭቱ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ማግኘት ይቻላል፣ ነገርግን ሁለቱም ወገኖች ጥፋት ከሚያስከትሉ ጉዳዮች መውጣት አለባቸው ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የእስራኤል የጸጥታ ካቢኔ የጋዛ ከተማን ለመቆጣጠር የቀረበውን እቅድ ማፅደቁን ተከትሎ ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እስራኤል ወታደራዊ እንቅስቃሴ ማስፋፋቷ፣ በፍልስጤም ንፁሃን ዜጎች እና በእስራኤል ታጋቾች ላይ ከፍተኛ ችግር ያስከትላል ሲል አስጠንቅቋል።

የእስራኤል ካቢኔ ውሳኔ በህይወት ያሉ እስራኤላውያን ታጋቾችን አደጋ ላይ እየጣለ እና ስቃያቸውን እያራዘመ ነው ሲሉ የታጋች ቤተሰቦች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የእስራኤል የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ በበኩሉ፣ የእስራኤል የጸጥታው ካቢኔ የጋዛ ከተማን ለመቆጣጠር ያሳለፈው ውሳኔ ወደ ከፍተኛ አደጋ የሚመራ ነው ብሎታል።

በእስራኤል ርዕሰ መዲና በቴልአቪቭም ትልቅ ህዝባዊ ተቃውሞ መቀስቀሱ ታውቋል።

የእስራኤል መንግስት ቢቢሲን ጨምሮ ዓለም አቀፍ የዜና ወኪሎች ጋዛ ውስጥ በነፃነት እንዲዘግቡ እንደማይፈቅድ ማሳወቁን ቢቢሲ ዘግቧል።

በብርሃኑ ወርቅነህ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review