ወጣቶች በኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ያላቸው ተሳትፎ እንዲያድግና በሀገር ጉዳይ ያገባኛል እንዲሉ እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው የ2017 በጀት አመት አፈፃፀሙን ገምግሞ በ2018 ዓ.ም በቅንጅት መስራት የሚያስችለውን የስምምነት ሰነድ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተፈራርሟል።
ለወጣቱ የሚሆኑ የልማት ስራዎችን ትኩረት ተሰጥቶበት ሲሰራበት የቆየና በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል ተግባር ስለመሆኑ ያነሱት የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በላይ ደጀን፣ ወጣቶች የተሰሩ የልማት ስራዎችን በመጠበቅና በመንከባከብ የባለቤትነት ሚና እንዲኖራቸው ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
ቢሮው ከ17 ተቋማት ጋር ለመስራት የስምምነት ሰነድ ስለመፈራረሙ ያነሱት አቶ በላይ፣ ስምምነቱም ወጣቱን ተጠቃሚ የሚያደርግ እና ሀገርን መገንባት የሚያስችል ነው ብለዋል ።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ወጣቱ በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎው የላቀ ነበርም ሲሉ አንስተዋል።
ትውልድ ላይ የሚሰራ ስራ በቅንጅት ፣ በትብብርና በጋራ የሚሰራ ስራ ነገ ውጤት የሚያመጣ ስለመሆኑ የስምምነት ሰነዱን የተፈራረሙት ባለድርሻ ተቋማት አንስተዋል፡፡
በቀጣይ በጀት ዓመት ሀገር ተረካቢውን ትውልድ የበቃ የማድረግና በተለያዩ ዘርፎች ተጠቃሚ እንዲሆን በሚያስችል ሁኔታም እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል፡፡
በፂዮን ማሞ