አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ መዲናዋን የሚመጥን ተወዳዳሪና ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ ለመሆን የጀመረዉን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ካሳሁን ጎፋ ገለጹ፡፡
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የ2017 በጀት ዓመት የስራ አፈፃፀም ግምገማና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ውይይት አካሄዷል፡፡
የኢዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ፣ ተቋሙ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከተሰጠው ተልእኮ አንጸር በርካታ እቅዶችን በተሻለ ሁኔታ ማከናወኑን ገልጸዋል፡፡
የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማትን ጨምሮ በመዲናዋ የተከናወኑ በርካታ የልማት ስራዎችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ከማድረግ ጀምሮ የአገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የበኩሉን ድርሻ መወጣቱን ገልጸዋል፡፡
በትውልድና ሀገረ መንግስት ግንባታ፣ ማህበራዊ እሴቶችን ከማጠናከር፣ ሰላምን ከማረጋገጥና ዴሞክራሲያዊ ባህሎችን በማስረጽ ረገድም ተቋሙ በርካታ ስራዎችን ማከናወኑን አቶ ካሰሁን ጎንፋ ተናግረዋል፡፡
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በመዲናዋ የተከናወኑ ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ሁነቶችን በቀጥታ ስርጭት ጭምር ለህብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ ሀገራዊ ድርሻውን መወጣቱንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የቋንቋ ብዝሃነትን ባማከለ መንገድ የተለያዩ የሚዲያ አማራጮችን፤ ቴክኖሎጂዎችን እና ብቃት ያለውን የሰው ኃይል በመጠቀም የከተማዋን እድገት የሚመጥን ሚዲያ ለመሆን አልሞ በመስራት ላይ እንደሚገኝም አስገንዝበዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2017 በጀት ዓመት ባካሄደው የስራ አፈጸጸም ምዘና፣ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ልዩ ተሸላሚ መሆኑ የበለጠ እንድንሰራ የማስፈንጠሪያ አቅም ሆኖናል ያሉት ዋና ስራ አስፈጸሚው፣ ተጨማሪ ይዘቶችንና ቴክኖሎጂዎችን በመታጠቅ ጭምር የተገኘውን ዉጤት ለማስቀጠል እንሰራለን ብለዋል፡፡
በዜና፤ በትምህርት ሰጪ ፕሮግራሞች፤ በመዝናኛ፤ በዲጂታል ሚዲያና ሌሎች ዘርሮች የጀመራቸዉን አበረታች ስራዎች በተሻለ ጥራትና አቀራረብ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ትክክል ያልሆኑና ሃሰተኛ መረጃዎችን በማጥራትና በማረም የከተማዋ ህዝብ ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኝ የተጀመረው ስራም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በመርሃ ግብሩ ማጠቃለያ በተጠናቀቀዉ የበጀት አመት የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ የተቋሙ ሰራተኞች እዉቅና ሰጥቷል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ