በብራዚል በቅርቡ በተካሄደው የወተት ውድድር ላይ ጊሮላንዶ የተሰኘችው የላም ዝሪያ በ3 ቀናት ውስጥ 343 ሊትር ወተት በመስጠት በሀገሪቱ ብሔራዊ ክብረወሰን ባለቤት ለመሆን በቅታለች፡፡
የተሻሻሉ ዝሪያዎች ድቅል የሆኑት የጊሮላንዶ ዝሪያ ላሞች ከፍተኛ በሆነ የወተት ምርት ይታወቃሉ፡፡
ዝሪያው በደቡብ አሜሪካ ሀገራትም በስፋት የሚገኝ ነው፡፡
እያንዳንዱ የጊሮላንዶ ላም በ305 ቀናት ውስጥ በዓማካይ 3 ሺህ 600 ሊትር ወተት ምርት ይሰጣሉ፡፡
አንዳንዶቹ ደግሞ ከዚህ በተለየ መልኩ በአንድ ቀን ብቻ ከ100 ሊትር በላይ ወተት እንደሚያመርቱ ይገለፃል፡፡
የብራዚል አርብቶ አደሮች በተለይም ላሞቻቸው በወተት ውድድር ወቅት አሸናፊ ሆነው ሲገኙ ወደር የሌለው ኩራት ነው የሚሰማቸው፡፡
ለዚህም ከውድድሩ በፊት ላሞቻቸው የተሻለ ወተት እንዲሰጡ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ያደርጋሉ፡፡
ከሰሞኑም ዴልፊም ሞሬራ በተባለ ቦታ በተካሄደው ወድድር ላይ በ3 ቀናት 343 ሊትር ወተት ያመረተች ላም አሸናፊ ሆናለች፡፡
በብራዚል ብሔራዊ የወተት ምርት ክብረወሰን ለመያዝም ችላለች፡፡
የላሟ ስምና ባለቤት እስካሁን ባይገለፅም በአሁኑ ሰዓት ላሚቱ በአንድ ቀን 120 ሊትር ወደማምረት መሸጋገሯን አዲቲ ሴትንትሯል ዘግቧል፡፡
ይህም በአንድ ቀን የወተት ምርት ክብረወሰን በሚል ተመዝግቦ ከሚገኘው ጋር መቀራረቡ ተገልጿል፡፡
በፈረንጆቹ 2019 የጊሮላንዶ ላም ዝሪያ የሆነችው ማሪሊያ ኤፍ አይ ቪ ቲያትሮ ዴ ናይሎ የተሰኘች ላም በአንድ ቀን 127.6 ሊትር ወተት በማምረት ክብረወሰኑን ጨብጣ ትገኛለች፡፡
በማሬ ቃጦ