•ከ4 ኪሎ እስከ እንጦጦ የተሰራው የኮሪደር ልማት ነባሮቹን የቱሪዝም መዳረሻዎች አጉልቶ ከማሳየት ባሻገር አዳዲስ ገፅታዎችንም ስለመፍጠሩ ተመላክቷል
በማለዳው እንጦጦ ተራራ ላይ ቆሜያለሁ፡፡ ተናፋቂዋ የክረምት ፀሐይ የከበባትን ደመና እየገፈታተረች ብቅ ብላለች፡፡ ከአራት ኪሎ ተነስቼ እዚህ ስፍራ እስክደርስ ከተሜው በግራና በቀኝ በወገባቸው ላይ ነጭ ቀለምን በቀጭኑ በተቀቡ፣ ዳርና ዳራቸውን ደግሞ በቢጫ ቀለም ባስዋቡ የእግረኛ መንገዶች ዘና ብሎ ገሚሲ ነፍሱን ከፈጣሪ፣ ገሚሱ ደግሞ ስጋውን ከጤናው ሊያስታርቅ ሽር ብትን ይላል፡፡
እናም እንጦጦ የደረስኩት ይህን ሁሉ ወፈ ሰማይ በቅርቡ ከተመረቀው ሸበላ መንገድ ጋር በወፍ በረር እየተመለከትኩ ነው፡፡ እኔ ያለሁበት የእንጦጦ ተራራ መልከ ብዙ ነው። ሰው ከራሱ ጋር የሚታረቅበት የተፈጥሮ ሸንጎ፣ ነፍስ ከፈጣሪዋ የምትስማማበት የፍቅር አደባባይ፣ ወዲህ ደግሞ እንደ ከረመ ወይን እያደር የሚጣፍጠው የአዲስ አበባ ቱባ ታሪክ እንደ ሀገር የሚመዘዝበት ዳጎስ ያለ ድርሳን ነው እንጦጦ፡፡
ለዚህ ደግሞ ከ1979 ዓመተ ምህረት ጀምሮ አገልግሎት እየሰጠ ያለው ሙዚየም አንዱ ምስክር ነው፡፡ በዚህ ሙዚየም ውስጥ ወዙ ያልነጠፈ፣ እውነታው ያልጎደፈ ታሪክ፣ ለዛና ደርዝ ያላቸውን ቅርሶች ተጎናፅፎ ይገኛል፡፡ ያለነው ከፍ ባለው ስፍራ፣ የምንጨዋወተው ህብረ ብሔራዊት ስለሆነችው አዲስ አበባ ነውና ከሙዚየሙ አያሌ ቅርሶች መካከል አንዲት ሰበዝን እንምዘዝ፡፡
ይሄውም በዓድዋ ጦርነት ጊዜ አጼ ምኒልክ “ምታ ነጋሪት ክተት ሰራዊት” ብለው ህዝቡን የቀሰቀሱበት ነጋሪት ከነ መጎሰሚያው በዚህ ሙዚየም ስለመኖሩ ጠቅሰን እንለፍ፡፡ ከዚህ ባሻገር በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደተፈለፈለ የሚነገርለት የእንጦጦ ዋሻ፣ የአጼ ምኒልክ ቤተ መንግስት፣ እንደ እንጦጦ ራጉኤልን የመሳሰሉ አብያተ ክርስቲያናት እና ልዩ ልዩ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ቅርሶች በእንጦጦ አካባቢ ይገኛሉ፡፡
እንጦጦ በ3 ሺህ 200 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኝ የአዲስ አበባ የራስ ቅል የሆነ ስፍራ ነው፡፡ ከፍ ያለው የአዲስ አበባ ታሪክም በዚህ አካባቢ ይገኛል ይላሉ የቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያው አቶ ሄኖክ አለሙ፡፡ በርግጥም እንጦጦ የአዲስ አበባ ልብሷ ብቻ ሳይሆን ነፍሷ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህም በመሆኑ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኝዎች ወደዚህ ስፍራ ሲመጡ እጅግ ይደሰታሉ፡፡
አሁን ደግሞ ከአራት ኪሎ እስከ እንጦጦ ያለው መንገድ ምቹ በሆነ መልኩ በኮሪደር ልማት አማካኝነት መገንባቱ፣ ከመንገድ ባሻገርም በተለያዩ ነገሮች ተሸፍነው የነበሩ ታሪካዊ ስፍራዎች ገለጥ ገለጥ ማለታቸውና በጥቂት እርምጃዎች ርቀት ውብ የመዝናኛ ስፍራዎች መገንባታቸው የጎብኝዎችን መንፈስ በማደስ ወደ መስህብ ስፍራዎቹ ሳይቸገሩ የሚንቀሳቀሱበትን ዕድል እንደሚፈጥርም አስጎብኝው ሄኖክ አለሙ ይገልፃሉ፡፡
እንጦጦ ተራራ ላይ ሆኖ አዲስ አበባን ቁልቁል ለተመለከታት ክዋክብት በውበቷ ተማርከው ዝቅ ያሉላት ትመስላለች። አካባቢው ነፋሻማ አየሩን እንደ እርጎ እየማጉ በቅርቡ ከተገነባው የእንጦጦ ፓርክ በረከቶች አንጀትን እያረሰረሱ እና አብዛኛውን የከተማዋን ክፍል ከርቀት እያማተሩ ዘና የሚሉበት ስፍራ ነው። አሁን ደግሞ መንገዱ በዘመነ መልኩ በኮሪደር ልማት በመሰራቱ ወደ አካባቢው የሚመጣው ሰው እየጨመረ መሆንን እንደታዘበ በስፍራው ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ያገኘሁት ወጣት ቴዎድሮስ ታፈረ አጫውቶኛል፡፡
ከእንጦጦ እስከ 4 ኪሎ ያለው መስመር የከተማዋ የቱሪዝም ፈርጦች በብዛት የሚገኙበት ስፍራ ነው፡፡ ለአብነትም የድል ሐውልት፣ ብሔራዊ ሙዚየም፣ የካቲት 12 መታሰቢያ ሐውልት፣ አንጋፋው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች አልባሳት ተሸምነው የሚቀርቡበት የሽሮ ሜዳ ገበያ፣ ዕድሜና ታሪክ ጠገብ የዕምነት ተቋማት እና ልዩ ልዩ የመስህብ ስፍራዎች ይገኙበታል፡፡ ይሁን እንጂ ቀደም ሲል መንገዱ ለተሽከርካሪም ሆነ ለእግረኛ አስቸጋሪ በመሆኑ እነዚህን ስፍራዎች በቀላሉ ለመመልከት ያስቸግር እንደነበር አስጎብኝው ሄኖክ አለሙ ይናገራሉ፡፡

ትንቢት ምግባርን ይቀድማልና አዲስ አበባ ፀጉሯን ተፈትታ ሹርባ እንደምትሰራ የገጠር ኮረዳ ውበቷ ከስሟ ጋር እየገጠመ ስለመሆኑ ወደ መዲናዋ ጎራ ያሉ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ሳይቀር በመመስከር ላይ ናቸው፡፡ በተለይ የኮሪደር ልማቱ ማራኪ ገፅታን እያላበሳት እንደሆነ በሽሮ ሜዳ አካባቢ ያገኘነው እና አዲስ አበባን ለዓመታት ያህል እንደተመላለሰባት ያጫወተን አሌክሳንደር ፒተር ከተማዋን እንዲህ ይገልፃታል፡፡ “Addis Ababa shines like the sun almost every day. It is growing immensely — truly amazing.” (ከተማዋ በየዕለቱ በሚባል ደረጃ እንደ ፀሐይ እያበራች እና ከዘመኑም ጋር እየተወዳጀች በሚገርም ለውጥ ውስጥ ትገኛለች፡፡) እንደማለት ነው፡፡
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝምና መስተንግዶ ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ኃላፊ እና መምህር ደመቀ ክብሩ እንደገለፁት፣ የኮሪደር ልማቱ በመዲናዋ የተገነቡ የቱሪዝም መስህቦችን በማገናኘትና የጎብኝዎችን እንግልት በመቀነስ ከተማዋን በጎብኝዎች ተመራጭና ዓለም አቀፍ የቱሪዝም መዳረሻ እያደረጋት ነው፡፡
አብዛኛዎቹ የዓለማችን ትላልቅ ከተሞች የቱሪዝም መዳረሻዎች መሆናቸውን ያወሱት የቱሪዝም ምሁሩ ለምሳሌ ኒውዮርክ፣ ፓሪስ እና ዱባይ ትላልቅ የቱሪስት መዳረሻ ከተሞች ናቸው፡፡ ይሄውም ያላቸውን ሀብት በስርዓቱ ማልማትና ማስተዋወቅ በመቻላቸው ነው ብለዋል፡፡
አንድ ቱሪዝም አምስት ወሳኝ ነገሮች ሊኖሩት ይገባል፤ የመጀመሪያው ትራንስፖርት ነው፡፡ ይሄውም አንድ ሰው ቱሪስት እንዲባል ከሚኖርበት አካባቢ ቢያንስ 80 ኪሎ ሜትር መጓዝ እንዳለበት ዓለም አቀፍ መስፈርቱ ያስቀምጣል፡፡ ለዚህ ደግሞ ግዴታ ትራንስፖርት ያስፈልገዋል። በመሆኑም የትራንስፖርት ዘርፉ የግድ ለቱሪዝም ምቹ መሆንን ይጠይቃል፤ ይህም በመሆኑ የኮሪደር ልማቱ በትራንስፖርቱ ዘርፍ ያለውን ችግር የሚቀርፍ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በዓለማችን እንደ ባንኮክ፣ ፓሪስ፣ ለንደን፣ ዱባይ፣ ሲንጋፖር እና ኢስታንቡልን የመሳሰሉ ከተሞች በበርካታ ቱሪስቶች የመጎብኘታቸው ምስጢር ለከተማ ቱሪዝም ምቹ መደላድል በመፍጠራቸው ነው፡፡ አዲስ አበባ ምንም እንኳ የአፍሪካ መዲና፣ ሶስተኛዋ የዲፕሎማሲ ከተማ እና የተለያዩ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት መቀመጫ ብትሆንም ለስብሰባና ለተለያዩ ጉዳዮች ወደ ከተማዋ የሚጎርፈውን ቱሪስት እስከ 3 እና 4 ቀናት ማቆየት አትችልም ነበር፡፡ ይህንን እውን ለማድረግ መንግስት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ በመሆኑ ቱሪስቱን ማቆየት የሚያስችሉ ልማቶች በከተማዋ እየተገነቡ ነው፡፡ ከ4 ኪሎ እስከ እንጦጦ ያለውም መንገድ ነባሮቹን መዳረሻዎች አጉልቶ ከማሳት ባሻገር አዳዲስ ገፅታዎችንም የተላበሰ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡
አክለውም በአፍሪካ በተለይም በምስራቅ አፍሪካ እንደ ኬኒያን የመሳሰሉ ጎረቤት ሀገራት ከኢትዮጵያ ያልተሻለ የቱሪዝም ሀብት ሳይኖራቸው ነገር ግን እንደ መንገድ ያሉ መሰረተ ልማቶችን በማሟላታቸው፣ ያላቸውን በማስተዋወቃቸው እና በመስራታቸው በብዙ እጥፍ ተጠቅመዋል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአዲስ አበባ ከተማም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች ለቱሪዝም ዘርፉ የተሰጠው ትኩረት የበለጠ ጠቀሜታ ያለው እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
በተለይም ለአዲስ አበባ ቱሪዝም እንቅስቃሴ እየተሰጠ ያለው ትኩረት በብዙ መልኩ ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን የተናገሩት የቱሪዝም ምሁሩ ከተማዋ ለቱሪዝም ምቹ በሆነች ቁጥር ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡ ጎብኝዎች ይበዛሉ፡፡ ይህ ደግሞ ገፅታችንን በዓለም አደባባይ በተሻለ መልኩ መገንባት ያስችለናል፡፡ በዓለም ጥሩ ዝና ሲኖረን ሌሎች ተጨማሪ ጎብኝዎች ይመጣሉ፡፡ ይህ ደግሞ ሰፊ የስራ ዕድልን፣ የውጭ ምንዛሬን እና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን ያስገኛል፡፡ ከዚህ አለፍ ሲልም በሀገራችን እና በታሪካችን የበለጠ እንድንኮራ እንደሚያደርገንም ጠቅሰዋል፡፡
እንደ መምህር ደመቀ ገለፃ፣ የኮሪደር ልማቱ አዲስ አበባን ከቱሪስቶች መሸጋገሪያነት ወደ መዳረሻነት ለመቀየር በሚደረገው ጥረት ውስጥ ያለው ድርሻ ከፍ ያለ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የቱሪስቱን ቀልብ የሚስቡ እንደ አንድነት፣ እንጦጦ፣ ወዳጅነት፣ የዓድዋ እና የሳይንስ ሙዚየምን የመሳሰሉ የቱሪስት መዳረሻዎች ተገንብተዋል፡፡
በሌላ በኩልም ዘመናዊ መንገዶች እየተገነቡ ነው፡፡ ይህም ጎብኝው ያለምንም መጨናነቅ በቀላሉ ከአንዱ ጫፍ ወደ ሌላኛው ጫፍ እየተንቀሳቀሰ መጎብኘት እንዲችል የሚያደርጉ በመሆናቸው የቱሪስቱን እንግልት መቀነስ ከመቻላቸው ባሻገር እንደ ሀገርም ከጎብኝዎች የሚገባንን ኢኮኖሚያዊም ሆነ ሌሎች ጥቅሞችን በሚገባ እንድናገኝ ያስችሉናል፡፡
ለቱሪዝም ዘርፉ ከሚያስፈልጉ ሌሎች መሰረታዊ ነገሮች መካከል በዋናነት ሦስቱ ሊሟሉ ይገባል ያሉት የቱሪዝም ምሁሩ አንዱ የቱሪስቱን ደህንነት መጠበቅ ነው፡፡ ስለሆነም ቱሪስቱ ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላው መስህብ ስፍራ ሲንቀሳቀስ ሳይንገላታ መሆን አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ የኮሪደር ልማቱ ትልቅ አበርክቶ አለው፡፡ ሌላው አገልግሎቶቻችን ንፅህናቸውን የጠበቁ እና ምቾት ያላቸው መሆን ስላለባቸው የኮሪደር ልማቱ ቱሪስቱ ሳይንገላታ፣ ምቾቱ ተጠብቆ እና ደስታ ተሰምቶት እንዲሄድና ተመልሶ እንዲመጣም የሚያደርግ ነው፡፡ በቅርቡ የተመረቀው ከ4 ኪሎ እስከ እንጦጦ የሚዘልቀውም መንገድ ይህንን የሚመሰክር እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
“አዲስ አበባማ አዲስ አበባማ፣
ሽርነው በጫማ” እንዳለው ዘፋኙ በስተቀኝ እና በስተግራ ውብ መልክዓ ምድር፣ ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናትን እና እንደ እንጦጦ ፓርክ ያሉ ዐይነ ግቡ መናፈሻዎችን ከፊት ለፊቴ ደግሞ እንደ አዲስ በልማት የተወለደችውን ከተማ ከርቀት እያየሁ እና የቱሪዝም ባለሙያውን ሀሳብ እያሰላሰልኩ ሽሮ ሜዳ ጫፍ ደርሻለሁ፡፡
በጉዞዬ ላይ ያገኘኋቸውና የአካባቢው ነዋሪ መሆናቸውን ያጫወቱኝ አቶ መሸሻ አማረ የቦታውን ጥንታዊ መታወቂያና መልክ ሳይለቅ በእንዝርት መልክ የተሰራውን ውብ የመናፈሻ ስፍራ በጣታቸው እያመላከቱ “አውላላው ሜዳ ላይ ሽንጧ እያረገደ፣
እንኳን እኔ ባዳው ወንድሟም አበደ። እንደሚባለው አብሬው እየዋልኩ ሰርክ ይናፍቀኛል” አሉኝ፡፡
በርግጥም ምቹ በሆኑት መንገዶች ዙሪያ ገባውን በመንፈስ እየዳሰስኩ ከ4 ኪሎ እስከ እንጦጦ ያደረኩት ጉዞ አዲስ አበባ ምን ያህል እንደ ንስር ከፍ ብላ እየታደሰች ስለመሆኑ በአርበ ልቦናዬ እንድታዘብ ዕድል ፈጥሮልኛል፡፡ በተለይ በቅርቡ የተመረቁት የተሽከርካሪ እና የእግረኛ መንገዶች እንዲሁም በዙሪያቸው ያሉ መናፈሻዎችና ልዩ ልዩ የዐይንም የቀልብም ማረፊያዎች ናቸው፡፡
በቱሪዝምና ቅርስ አስተዳደር መስክ ሰፊ ምርምሮችን ያደረጉት ከተሞች፣ ቅርሶች እና ቱሪዝም ያላቸውን ግንኙነቶች በተለይም የከተማ ቦታዎችን ከባህላዊ እና ታሪካዊ ሀቆች ጋር እንዴት ማጣጣም እንደሚቻል በጥናታቸው ካረጋገጡ እውቅ የከተማ ልማት፣ ቱሪዝምና ቅርስ አስተዳደር ምሁራን መካከል እንግሊዛዊው አንቶኒ ጂ አሽዎርዝ (ፕሮፌሰር) እንዲህ ይላሉ “መንገዶች የከተሞች ፍካት፣ የደም ስሮች እና እስትንፋሶች ናቸው፡፡ ከተማና ቱሪዝምን ከመንገድ መነጠል ደግሞ ውሃ ውስጥ ሻማ እንደመለኮስ ነው፡፡”
በመለሰ ተሰጋ