“ለበለጠ የህዝብ አገልጋይነት እንድንተጋ የሚያነሳሳ ነው“
በአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ እውቅናና ሽልማት የተሰጣቸው ሰራተኞችና አመራሮች
ለተቋማት ስኬት የአመራሮችና ሰራተኞች የተጣለባቸውን ኃላፊነት በተነሳሽነት፣ በትጋትና በጋራ የመከወን አቅም ወሳኝነት አለው፡፡ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በቅርቡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባካሄደው የ2017 በጀት ዓመት የስራ አፈፃፀም ምዘና፣ በህዝብና መንግስት መካከል ድልድይ በመሆን በሰራው ስራ ልዩ ተሸላሚ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ከተለያዩ ተቋማት በተለያየ ጊዜ እውቅና ማግኘቱም ይታወሳል፡፡
ከትናንት በስቲያ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የ2017 በጀት ዓመት አፈፃፀምና የ2018 ዕቅድ ላይ ውይይት ባደረገበት ወቅት ለስኬታማነቱ ጉልህ አስተዋፅኦ ለነበራቸውና የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ አመራሮችና ሰራተኞች እውቅና እና ሽልማት አበርክቷል፡፡
በዕለቱ እውቅና ከተሰጣቸው መካከል በቴሌብዥን ዘርፍ የወቅታዊ ጉዳዮች ዋና አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ አላዓዛር መኮንን ባገኘው እውቅና መደሰቱን ተናግሯል፡፡ “በተቋሙ ብዙ ዓመት እንደቆየ ሰራተኞች ቀደም ሲል ሚዲያው ምን ደረጃ ላይ እንደነበር አውቃለሁ፡፡ ዛሬ ላይ በከተማም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተፅዕኖ እየፈጠረ፣ እያደገና እየተለወጠ መጥቷል፡፡ ተቋሙ እያስመዘገበ ላለው ውጤት `ትልቅ አበርክቶ አድርጋችኋል’ ተብለን እውቅና ማግኘታችን ቀላል ነገር አይደለም∫ ብሏል፡፡
ጋዜጠኛ አላዓዛር የሚያዘጋጀው ™አገልጋይ∫ የተሰኘው ፕሮግራም መቅረብ ከጀመረ ጊዜ አንስቶ በርካታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በተለይም የመልካም አስተዳደርና ብልሹ አሰራሮችን በመለየት፣ በማጋለጥና መፍትሔ እንዲገኝ በማድረግ በመንግስትና በህዝብ መካከል እንደ ድልድይ በመሆን የራሱ የሆነ አዎንታዊ አስተዋፅኦ ማበርከቱን አንስቷል፡፡
ሌላኛው ባገኘው እውቅናና ሽልማት ደስታ እንደተሰማው የገለፀልን በኤ ኤም ኤን ፕላስ የአፋን ኦሮሞ ክፍል ጋዜጠኛ መንገሻ ዳርጌ ነው፡፡ የ2017 በጀት ዓመት አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ውጤታማ ስራዎችን ያከናወነበት ዓመት ነው፡፡ እንደ አፋን ኦሮሞ ደግሞ አዲስ በተጀመረው ኤ ኤም ኤን ፕላስ የህዝብን ፍላጎት ታሳቢ ያደረጉ የተለያዩ የፕሮግራም ፎርማቶችን በመቅረፅ ለህዝብ ማድረስ ተችሏል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ `የተሻለ አስተዋፅኦ አበርክተሃል’ በሚል የተሰጠኝ እውቅና ሽልማት ከዚህ በላይ መስራት እንዳለበኝ ኃላፊነት የሚጥል እንደሆነ ተናግሯል፡፡ እውቅና ሽልማቱ በሰራተኞች መካከል ጤናማ የውድድር መንፈስ በመፍጠር ተቋሙ ያቀዳቸውን ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ አቅም እንደሚሆንም ገልጿል፡፡
™ሽልማቱ የእኔ ብቻ ሳይሆን የባለሙያዎች ጭምር ነው∫ ያሉት ደግሞ በተቋሙ የገቢ አሰባሰብና ክትትል ዲፓርትመንት ኃላፊ ወይዘሮ አገሪቱ ቢተው ናቸው፡፡ በ2016 በጀት ዓመት 157 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ ተችሎ ነበር፡፡ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በትጋትና በመግባባት በመስራት 149 ሚሊዮን ለመሰብሰብ አቅደን ከታቀደው በላይ 261 ሚሊዮን ብር አካባቢ በመሰብሰብ የተቋሙን ገቢ ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በኤ ኤም ኤን፤ ኤፍ ኤም 96.3 ትምህርታዊ ይዘት ዘርፍ ውስጥ የምትሰራው ጋዜጠኛ ሀይማኖት ግዛቸውም በተሰጣት እውቅና እና ሽልማት ደስተኛ መሆኗን ተናግራለች፡፡ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የአሁኑን ስያሜ ከመያዙ በፊት ቀደም ባሉት ዓመታት ቴሌቭዥንን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ስትሰራ መቆየቷን ያነሳችው ጋዜጠኛ ሃይማኖት፣ በተለያዩ ጊዜያት በሚሰጡ የእውቅና እና የሽልማት ፕሮግራሞች ተሸላሚ እየሆነች መምጣቷንና አሁን የተሰጣትም ለበለጠ ትጋት ተነሳሽነትን እንደሚፈጥርላት ገልጻለች፡፡
እውቅናና ሽልማት ያገኙ ሰራተኞችና አመራሮች በተሰጣቸው እውቅና ሳይዘናጉ በቀጣይ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በተሻለ ለመወጣት እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡
™በየትኛውም መስክ ተግቶ መስራት ውጤታማ ያደርጋል∫ የምትለው ጋዜጠኛ ሃይማኖት፣ እውቅና እና ሽልማቱ ሌሎችም ለመሸለም የበለጠ እንዲሰሩ ያደርጋል፡፡ ይህ አይነቱ መልካም ተግባር ባህል መሆን እንዳለበት ተናግራለች፡፡
™አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ እየተለወጠች ባለች ከተማ፣ እየተለወጠ ያለ ሚዲያ ነው፡፡ የከተማዋን መልክና ገፅታ ለመምሰል ጥረት በሚያደርግ ሚዲያ ውስጥ መስራት መታደል ነው፡፡∫ ያለው ጋዜጠኛ አላዓዛርም፣ ሚዲያው በሰው ሀይል፣ ቴክኖሎጂ፣ በአሰራርና አደረጃጀት እየተለወጠ የመጣ ተቋም እንደመሆኑ፣ እውቅናው ሰራተኛው ራሱን እያበቃ ለውጤት እንዲዘጋጅ ጉልበት ይሆናል፡፡ ቀጣይ ተቋሙ የያዛቸው ስትራቴጂያዊ ግቦች እንዲሳኩ እድል ይፈጥራል ብሏል፡፡
ወይዘሮ አገሪቱም፤ ™ባገኘሁት እውቅና እና ሽልማት በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ በቀጣይ የበለጠ ለመስራት ትልቅ ኃላፊነት ነው የተሰጠኝ∫ ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ሚዲያው በሁሉም መስክ ላስመዘገበው ውጤት የተቋሙ አመራርና ሰራተኞች የላቀ ሚና መጫወታቸውን ያነሱት የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ በበኩላቸው፣ በቅርቡ እንደከተማ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ልዩ ተሸላሚ መሆኑ የሚያዘናጋ ሳይሆን የበለጠ እንድንሰራ የማስፈንጠሪያ አቅም የሚሆን ነው፡፡ ሚዲያው የመዲናዋን እድገት የሚመጥን፣ ተወዳዳሪና ተመራጭ ሆኖ እንዲቀጥል የእያንዳንዱ ዘርፍ ተቀናጅቶ መስራቱን አጠናክሮ ማስቀጠል አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ከአመራርና ሰራተኛው ከፍ ያለ ኃላፊነት እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል፡፡
በዕለቱ ለአመራሮችና ሰራተኞች እውቅና እና ሽልማት ከመስጠት በተጨማሪ የተቋሙ የ2017 በጀት ዓመት የስራ አፈፃፀም ግምገማና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ውይይት ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡ የተጠናቀቀው በጀት ዓመት አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ አመርቂ ስራዎች ያከናወነበት እና እምርታዊ ውጤቶችን ያስመዘገበበት ነው፡፡ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማትን ጨምሮ በመዲናዋ የተከናወኑ በርካታ የልማት ስራዎችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ከማድረግ ጀምሮ የአገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የበኩሉን ድርሻ ተወጥቷል፡፡ በትውልድና ሀገረ መንግስት ግንባታ፣ ማህበራዊ እሴቶችን በማጠናከር፣ ሰላምን በማረጋገጥና የዴሞክራሲ ባህልን በማስረጽ ረገድም በርካታ ስራዎችን አከናውኗል፡፡
በመዲናዋ የተከናወኑ ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ሁነቶችን በቀጥታ ስርጭት ጭምር ለህብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ ሀገራዊ ድርሻውን ተወጥቷል፡፡ የቋንቋ ብዝሃነትን ባማከለ መንገድ የተለያዩ የሚዲያ አማራጮችን፤ ቴክኖሎጂዎችን እና ብቃት ያለውን የሰው ኃይል በመጠቀም የከተማዋን እድገት የሚመጥን ሚዲያ ለመሆን አልሞ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ዋና ስራ አስፈጻሚው አስገንዝበዋል፡፡
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በሁለት የቴሌቪዥን ቻናሎች (AMN እና AMN+)፣ በሬድዮ ኤ ኤም ኤን ኤፍ ኤም 96.3፣ በዲጂታል ሚዲያና በአዲስ ልሳን ጋዜጣ አማራጮቹ መረጃዎችን በፍጥነት፣ በጥራት እና በስፋት ለህዝብ እያደረሰ ይገኛል፡፡
በስንታየሁ ምትኩ