“ ከሰኔ 5 እስከ ጳጉሜ 5 ድረስ 340 ሺህ የሚሆኑ የፋይዳ መታወቂያ ያላቸውን ተማሪዎች ለመመዝገብ አቅጄ እየሰራሁ ነው”
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ
የክረምት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ ባሕረ ሐሳብ በተሰኘው የፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ መፅሐፍ ላይ እንደተመላከተው፤ በአራት ወቅቶች በሚከፋፈለው የኢትዮጵያዊያን አንድ ዓመት ውስጥ፤ ከሰኔ 26 እስከ መስከረም 25 ያለው ጊዜ “ክረምት” በመባል ይታወቃል፡፡ ይህ ወቅት ለትምህርት ተቋማት ሁለት መሠረታዊ ተግባራትን የሚከውኑበት ነው፡፡ የ2017 የትምህርት ዘመንን የሥራ እንቅስቃሴ አገባድደው ተማሪዎቻቸውን ለተወሰኑ ጊዜያት ለእረፍት የሚሸኙበት ሲሆን፤ በተመሣሣይ የ2018 የትምህርት ዘመንን በአዲስ መንፈስ እና መነቃቃት ተማሪዎቻቸውን ለመቀበል እና የመማር ማስተማር ሥራውን ለማከናወን የሚያስችላቸውን የዝግጅት ምዕራፍ የሚያጠናቅቁበት ነው፡፡
በመዲናችን አዲስ አበባ የሚገኙ የትምህርት ተቋማት በክረምቱ ወቅት የሚከናወኑ ወሳኝ ተግባራትን ፈፅመዋል፤ በመፈፀምም ላይ ይገኛሉ። አሁን በምንገኝበት የክረምቱ ወቅት እኩሌታ ላይ፤ ትምህርት ቤቶች ነባር እና አዳዲስ ተማሪዎችን እየመዘገቡ ነው። በየአካባቢያችን በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ያለው እንቅስቃሴም ይህንን የሚያሳይ ነው፡፡ እኛም በተመለከትናቸው ትምህርት ቤቶች ያረጋገጠነውም፤ ወቅቱ የተማሪዎች የምዝገባ ጊዜ መሆኑን ነው፡፡ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤቶቹ ለምዝገባ ሲመጡ ማሟላት ከሚጠበቅባቸው መረጃዎች መካከል ማንነትን የሚገልፀው ሀገር አቀፍ “የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ ካርድ (ፋይዳ መታወቂያ)” ነው፡፡ ማንኛውም ተመዝጋቢ ተማሪ የፋይዳ መታወቂያን መያዝ ግዴታ ጭምር መሆኑንም መገንዘብ ችለናል፡፡
የጥበብ እድገት ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ2018 ትምህርት ዘመን እያከናወነ ያለውን የተማሪዎች ምዝገባ ሂደት ምን እንደሚመስል በአካል ተገኝተን ተመልክተናል፡፡ ለአዲሱ የትምህርት ዘመን ከሚከናወኑ ወሳኝ የዝግጅት ምዕራፍ ተግባራት መካከል አንዱ የሆነው የተማሪዎች ምዝገባ ሂደት እንዲሳካ ተማሪዎች፣ የተማሪ ወላጆች (አሳዳጊዎች)፣ መምህራን፣ የትምህርት ቤት አመራሮች እና የአስተዳደር ሰራተኞች ኃላፊነታቸውን ለመወጣት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የሚደነቅ ነው፡፡
ወይዘሮ ሣራ ጠብቄ፤ የተማሪ ፂዮን ዘውዱ ወላጅ እናት ናቸው። በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ የመገኘታቸው ምክንያት በ2018 የትምህርት ዘመን የስምንተኛ ክፍል ትምህርቷን የምትከታተለውን ልጃቸውን ለማስመዝገብ ነው፡፡ እሳቸው ወደ ትምህርት ቤቱ የመጡት የዲጂታል መታወቂያ ካርድ (ፋይዳን) ጨምሮ ለምዝገባ የሚያስፈልጉ መረጃዎችን ቀድመው በማዘጋጀት እና በመያዝ ነው፡፡ በዚህም ምዝገባውን ያለአንዳች መስተጓጎል በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ ችለዋል፡፡ የዛሬ ዓመት ገደማ ለልጃቸው የፋይዳ መታወቂያ ማውጣት መቻላቸው ካለምንም እንግልትና መመላለስ ጉዳያቸውን ፈፅመው ለመውጣት እንዳስቻላቸው የተናገሩት ወይዘሮ ሣራ፤ ባለቤታቸው የሚሠሩበት የኢትዮ ቴሌኮም ተቋም ለፋይዳ መታወቂያ ተደራሽነት ቀድሞ ወደሥራ የገባ መሆኑ የተማሪዋ የፋይዳ መታወቂያ የሰባተኛ ክፍል ትምህርቷን እየተከታተለች ባለችበት ጊዜ እንዲወጣ ማስቻሉን አስረድተዋል፡፡
“ልጆቻችን ማንነታቸውን የሚገልፅ መታወቂያ መያዛቸው ጥቅሙ በርካታ ነው” የሚሉት የተማሪ ፂዮን እናት፤ የፋይዳ መታወቂያ ከትምህርት ምዝገባ ባለፈ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልፀዋል፡፡ ይህንንም ጠቀሜታ በምሳሌ እንደሚከተለው አስረድተዋል፤ “ከትምህርት ቤት ወደ ቤት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ በመሃል የመጥፋት አጋጣሚ ይፈጠራል፡፡ ሰዎችን እርዳታ በሚጠይቁበት ወቅት ፋይዳ መታወቂያ ላይ ባለው መረጃ መሰረት ስልክ በመደወል በቀላሉ ተማሪና ወላጅ እንዲገናኝ ያግዛቸዋል፡፡”
በተመሳሳይ በትምህርት ቤቱ ያገኘናቸው ተማሪ አሜን አሸናፊ እና ወላጅ እናቱ ወይዘሮ መቅደስ ስዩምን ነው፡፡ በትምህርት ቤቱ የተገኙት የምዝገባ ሂደትን ለመፈፀም ነው፡፡ በ2018 የትምህርት ዘመን የሰባተኛ ክፍል ተማሪ የሚሆነውን ልጃቸውን ለማስመዝገብ ከአንድ ቀን በፊት መጥተው የነበሩት ወይዘሮዋ፤ ሲመጡ ማሟላት ከሚገባቸው መካከል የልጃቸውን ማንነት የሚገልፅ የፋይዳ መታወቂያ ስላልነበረው በዕለቱ ሳይስተናገዱ ቀርተዋል፡፡ እንደተመለሱ ግን ዋና ሥራቸው ያደረጉት ለልጃቸው የፋይዳ መታወቂያ ምዝገባ ማድረግ ነው። በዚሁ መሰረት ወዲያው አቅራቢያቸው ወደሚገኘው የኢትዮ ቴሌኮም ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት በማቅናት የመታወቂያ ምዝገባ አከናወኑ፡፡ ምዝገባውን ባከናወኑበት ዕለት በስልካቸው ምዝገባው በትክክል መከናወኑን የሚያረጋግጥ የፋይዳ ልዩ ቁጥር እንዲሁም የፋይዳ ተለዋጭ ቁጥር በአጭር የፅሁፍ መልዕክት ደረሳቸው፡፡ ይህንን ማስረጃ ይዘው በመምጣት ልጃቸውን ማስመዝገብ መቻላቸውን አብራርተዋል፡፡
የምዝገባ ሂደቱ በምን መልክ እየተከናወነ እንደሆነ ያነጋገርናቸው የትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህር ተወካይ እሱእንዳለ በቀለ፣ በ2018 ትምህርት ዘመን በትምህርት ቤቱ ምዝገባ ለማከናወን የሚመጡ አዲስ እና ነባር ተማሪዎች ምዝገባውን በተሳካ ሁኔታ ለመፈፀም ይዘው መምጣት ከሚጠበቅባቸው ሰነዶች አንዱ የፋይዳ መታወቂያ ነው፡፡ ይህ እንደ ሀገር የተቀመጠ የሥራ አቅጣጫን መሰረት አድርጎ ነው እየተተገበረ ያለው። በትምህርት ቤቱ፤ የቅድመ መደበኛ ተማሪዎችን ጨምሮ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ ያሉ ተማሪዎችን ተቀብሎ ያስተምራል፡፡ ይህ መረጃ እስከ ተሰበሰበበት ነሐሴ 2 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ትምህርት ቤቱ ከ860 በላይ የፋይዳ መታወቂያ ያላቸውን ተማሪዎች መዝግቧል፡፡
ተወካይ ምክትል ርዕሰ መምህሩ አክለው እንደገለፁት፤ በትምህርት ቤቱ የሚገኙ ተማሪዎች የፋይዳ መታወቂያ በመያዝ ምዝገባ እንዲያደርጉ በትምህርት ቤቱ ማስታወቂያ ሰሌዳዎች ላይ ተለጥፏል፤ በግሩፕ የቴሌግራም አድራሻ ላይም በየጊዜው በሚለቀቁ መልዕክቶች ተማሪዎች እና የተማሪ ወላጆች (አሳዳጊዎች) እንዲያውቁ ተደርጓል። ይህም አብዛኛው ለምዝገባ የሚመጣ ተማሪ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ይዞ እንዲመጣ አስችሏል፡፡ አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸውን የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ካደረጉ በኋላ የመለያ ቁጥሩ በስልካቸው በሚላክ መልዕክት ሳይደርሳቸው ለቀናት የሚዘገይበት አጋጣሚ መፈጠሩ ትምህርት ቤቱ በሚያከናውነው የተማሪዎች ምዝገባ ሂደት ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩን አልሸሸጉም። ይህንን ችግር ለመፍታት እንደትምህርት ቤት የተሄደበት ርቀት አለ፡፡ ይህም፤ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ከተመዘገቡ በኋላ በስልካቸው የሚደርሳቸውን ባለ አስራ ስድስት አሃዝ (ዲጂት) ቁጥር ይዘው መምጣት ባይችሉ፤ የተመዘገቡበትን ቁጥር ይዘው ከመጡ ተማሪዎቹ እንዲመዘገቡ ማድረግ ሲሆን፤ የመፍትሄ አማራጩ የወላጆችን እንግልት ቀንሷል፡፡
መሃል ግንፍሌ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤትም የ2018 የትምህርት ዘመን ተማሪዎቹን በመመዝገብ ሂደት ላይ ይገኛል፡፡ ትምህርት ቤቱ የምዝገባ ሂደቱን በምን አግባብ እያከናወነ እንደሚገኝ፣ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ጉዳይ በምን አግባብ ተፈፃሚ እየሆነ እንዳለ የትምህርት ቤቱን ምክትል ርዕሰ መምህርት ቅርስነሽ የማነብርሃንን አነጋግረናቸዋል። እሳቸው ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት ማብራሪያ፤ ለ2018 የትምህርት ዘመን ተማሪዎች ምዝገባ የሚያካሄዱት በፋይዳ መታወቂያ ብቻ ነው፡፡ ትምህርት ቤቱ የሚያስተምራቸውን ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ያሉ ነባር እና አዳዲስ ተማሪዎችን ተቀብሎ እየመዘገበ ይገኛል። የትኛውም ወላጅ ልጁን ለማስመዝገብ ሲመጣ ማሟላት ስለሚገባው ነገር በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ በር ላይ በጉልህ የተዘጋጀ ማስታወቂያ ተለጥፏል። በማስታወቂያው ላይ ከተጠቀሱት ለምዝገባ የሚያስፈልጉ ማስረጃዎች መካከል የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ አንዱ ነው፡፡ በማስታወቂያው መሰረት አስፈላጊውን ሁሉ ያሟሉ ተማሪዎች እየተመዘገቡ ነው፡፡ እስከ ነሐሴ 2 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ ትምህርት ቤቱ አንድ መቶ ሰላሳ ተማሪዎችን መዝግቧል፡፡
ምክትል ርዕሰ መምህርት ቅርስነሽ፤ “በሁሉም ትምህርት ቤቶች በሚከናወን የተማሪዎች ምዝገባ ላይ ተማሪዎች ሊያሟላቸው ከሚገቡ ማስረጃዎች አንዱ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ነው፡፡ ይህንን በማሟላት በወቅቱ ልጆቻቸውን የማስመዝገብ ትልቅ ኃላፊነት በወላጆች ላይ የወደቀ መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡ ኃላፊነታቸውንም ጊዜ ሳይሰጡ መፈፀም ይኖርባቸዋል” የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ አድርገው መታወቂያው ያልደረሰላቸው፤ የመለያ ቁጥርን የሚገልፀው የጽሑፍ መልዕክት በስልካቸው ከተላከላቸው ይህንን አይቶ ምዝገባውን ማካሄድ የሚቻልበት አግባብ ስለመኖሩም አስታውቀዋል፡፡
የመሃል ግንፍሌ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ነባር እና አዲስ ተማሪዎቹን እየመዘገበበት ባለው ሂደት ውስጥ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ አስፈላጊነትን እና የሚስተናገዱበትን አማራጮች አስመልክቶ በትምህርት ቤቱ ምክትል ርዕሰ መምህርት ከላይ የተገለፀው ሃሳብ በተግባር እየተፈፀመ ስለመሆኑ፤ ወደ ትምህርት ቤቱ ለመመዝገብና ለማስመዝገብ መጥተው ያገኘናቸው የተማሪ አቤል ረታ እና የወላጅ እናቱ የወይዘሮ መስከረም መንገሻ ሁኔታ ምስክር ነው፡፡
ወይዘሮ መስከረም ወደ ትምህርት ቤቱ የመጡት የ6ኛ ክፍል ተማሪ ልጃቸውን ለ2018 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ለማስመዝገብ ነው፡፡ እንደ ወይዘሮዋ ገለጻ፣ በእጃቸው ከያዟቸው አስፈላጊ ማስረጃዎች መካከል የልጃቸውን ማንነት የሚገልፅ የፋይዳ መታወቂያ አለመኖሩን መዝጋቢዎቹ አረጋገጡ፡፡ ከዚያም የመፍትሔ አቅጣጫ በማስረዳት አሟልተው እንዲመጡ መለሷቸው። እሳቸውም አቅራቢያቸው ወዳለ የግል ባንክ በማቅናት የፋይዳ መታወቂያ ምዝገባ ፈጸሙ፡፡ ይህም ሆኖ፤ እንደነዚህ ያሉ ወሳኝ ጉዳዮች ቀደም ብሎ መፈፀም እና በእጅ መያዝ ካላስፈላጊ እንግልት እንደሚታደግ ትምህርት የወሰዱበትን ልምድ አግኝተዋል፡፡
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የኮሚኒኬሽን እና የህዝብ ግንኙነት ማኔጅመንት ስፔሺያሊስት ወይዘሮ ሩት ሚካኤል የብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ (ፋይዳን) አስመልክቶ ለዝግጅት ክፍላችን እንዳስረዱት፣ ሀገራችን ወደ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን በምታደርገው ጉዞ ዋነኛው እና አንዱ ዓላማ በመንግስት እና በግል ዘርፉ በኩል ዲጂታላይዝድ የሆነ አገልግሎት መስጠት ነው። አገልግሎቶች ዲጂታላይዝድ በሆኑ ቁጥር ማህበረሰቡ የተሳለጠ አገልግሎት ማግኘት ይችላል። ይህ የሀብት ብክነትን ከመቀነስ በተጨማሪ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገልግሎት ሲሰጡ የግለሰብን ማንነት ለማጣራት የሚፈጅባቸውን ወጪ እና ጊዜ ይቀንሳል። ሰዎች ከየትኛውም ቦታ ሆነው በአካል መገኘት ሳይኖርባቸው አገልግሎትን እንዲያገኙ ያስችላል። ይህም መሆን የሚችለው ህጋዊ የሆነ ማንነት ሲኖራቸው ነው፡፡
ወይዘሮ ሩት በማብራሪያቸው፤ ከ3 እስከ 5 ዓመት ባለው ጊዜ 90 ሚሊዮን ዜጎችን የብሔራዊ ዲጂታል (ፋይዳ) መታወቂያ ለመመዝገብ ታቅዷል። እስከአሁን እንደ ሀገር ቁጥራቸው ከ21 ሚሊዮን በላይ የሚጠጉ ዜጎችን ለመመዝገብ ተችሏል። 55 ተቋማት አገልግሎታቸውን ከፋይዳ መታወቂያ ጋር አስተሳስረዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል የትምህርት ተቋም አንዱ ነው። ተማሪዎች ለ2018 የትምህርት ዘመን ምዝገባ ሲያከናውኑ “የፋይዳ መታወቂያ” ሊኖራቸው እንደሚገባ አቅጣጫ ወርዶ ተፈፃሚ በመሆን ላይ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በመዲናዋ በሚገኙ ባንኮች፣ በፖስታ ቤት፣ በሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ አገልግሎት፣ የኢትዮቴሌኮም የሽያጭ ማዕከላት፣ በወረዳ እና ክፍለ ከተማ፣ በገቢዎች ቢሮ በኩል እንዲሁም በክልል ከተሞች በገቢዎች ቢሮዎች በኩል ምዝገባ እየተካሄደ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ በየደረጃው የሚማሩ ተማሪዎች የፋይዳ መታወቂያ እንዲያወጡ የተፈለገበትን ምክንያት ወይዘሮ ሩት ሲያብራሩ፤ “በጊዜ ብዛት እና በሁኔታዎች ምክንያት የተዛባ የመረጃ ስህተት ያላቸው የትምህርት መረጃዎች እንዳይኖሩ፣ ከልጅነት እድሜያቸው በዲጂታል ኢኮኖሚው ስነ ምህዳር እንዲሁም ወጥ የሆነ የሲቪል ምዝገባ ስርዓት በመካተት (እንደ ልደት ምስክር ወረቀት እና ክትባት የመሳሰሉ) አገልግሎቶችን በአስተማማኝ ሁኔታ ለማግኘት፣ የልጆች የባንክ ሒሳብ በራሳቸው የተረጋገጠ ማንነት ለማውጣት የሚከወኑ ተግባራትን ለማቅለል እና ጥራት ያለው መረጃ እንዲኖር ለማድረግ አቅም ይፈጥራል፡፡ በዲጂታላይዜሽን ዘመን በስፋት የሚሰጡ የኦንላይን ስልጠናዎችን እና የትምህርት እድሎችን በሚያገኙበት ወቅት ትምህርቱን በአግባቡ እንዲከታተሉ፣ ከተከታተሉ በኋላ ወጥ የሆነ የትምህርት ማስረጃ እንዲኖራቸው፣ በልዩ ሁኔታ ራሳቸውን ለመለየት፣ የሀገር አቀፍ ፈተናዎች ላይ ቅድመ ሁኔታ ለማሟላት፣ የተሳለጠ የትምህርት አስተዳደር ለመገንባት እና በትምህርት ቤት የሚሰጡ አገልግሎቶችን ትክክለኛው ተማሪ እንዲያገኝ የሚያስችል መልካም ሁኔታዎችን የሚፈጥር ነው” በማለት ነው፡፡
እድሜው 5 ዓመት እና ከዚያ በላይ የሆነ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ አሻራ በመስጠት ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ (ፋይዳ) ምዝገባ መፈጸም ይችላል፤ ይጠበቅበታልም፡፡ ከ5 ዓመት በታች ለሆኑ ህፃናት በወላጅ ምስክር ብቻ ያለ ባዮሜትሪክስ (አሻራ) ሳይሰጡ መመዝገብ ይችላሉ። ይህም ለህፃናት ልደት እና ተያያዥ ሲቪል ምዝገባ ሲስተሞች ፋይዳ እንደ ልዩ ቁጥር ሆኖ እንዲያገለግል ይረዳል። ሆኖም ከ18 ዓመት በታች ያለ ማንኛውም ሰው ሲመዘገብ ወላጅ ወይም አሳዳጊ የፈቃደኝነት ቅፁን ሊፈርምለት እንደሚገባ የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የኮሚኒኬሽን እና የህዝብ ግንኙነት ማኔጅመንት ስፔሺያሊስቷ ወይዘሮ ሩት ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የስርዓተ ትምህርት ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው እታለማ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት፤ የፋይዳ መታወቂያ በአስገዳጅ ሁኔታ ተማሪዎች እንዲያወጡ እየተደረገ ነው። የፋይዳ መታወቂያ ያለው ተማሪ ብቻ በ2018 የትምህርት ዘመን መመዝገብ ይችላል፡፡ ቢሮው ከሰኔ 5 ጀምሮ እስከ ጳጉሜ 5 ድረስ 340 ሺህ የሚሆኑ የፋይዳ መታወቂያ ያላቸውን ተማሪዎች ለመመዝገብ በእቅድ ደረጃ ይዟል። ይህንን መረጃ እስካጠናቀርንበት ሐምሌ 25 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ 300 ሺህ የሚሆኑ ተማሪዎችን ለመመዝገብ ስለመቻሉ ተናግረዋል፡፡
ሁሉም ተማሪ የፋይዳ መታወቂያ ሲኖረው ብቻ ነው የሚስተናገደው፡፡ ለምዝገባው በቂ ጊዜ ያለ በመሆኑ ወላጆች ተገቢውን መረጃ አሟልተው በመገኘት ልጆቻቸውን ማስመዝገብ እንደሚችሉም አስታውቀዋል፡፡
እንደ ወ/ሮ ሩት ገለጻ፤ በተለይም ከዋናው ድህረ ገጽ id.et በተጨማሪ በሁሉም የማህበራዊ ሚዲያዎች በስፋት እንገኛለን፡፡ ልጆችንም በትምህርት ቤቶቻቸው አሊያም በአቅራቢያዎቻቸው የሚገኝ ምዝገባ ጣቢያ id.gov.et/locations ላይ በማየት እና የፈቃድ ቅፅ ላይ በመፈረም ማስመዝገብ እንደሚቻል ጭምር አስታውቀዋል፡፡
በሄለን ጥላሁን