የመጻሕፍት የጀርባ ገፅ ጽሑፍ ዓላማን ምንያህል ተረድተነዋል?

You are currently viewing የመጻሕፍት የጀርባ ገፅ ጽሑፍ ዓላማን ምንያህል ተረድተነዋል?

ዋለልኝ አየለ በተለያየ ጊዜ የገዛቸው በርካታ መጻሕፍት አሉት፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ አንባቢ ነው፡፡ ሁሉንም ባይሆንም አንዳንዶችን መጽሐፍት የገዛቸው የጀርባ አስተያየት (ብለርብ) አይቶ ነው፡፡ የጀርባ አስተያየት ላይ ያለውን ትዝብት ሲያጋራም፣ “አንዳንድ ጊዜ ሚዛናዊ አስተያየትና የመጽሐፉን የውስጥ ይዘት የሚገልጽ ሆኖ አገኘዋለሁ፡፡ አንዳንዱን ደግሞ እንደጠበቅኩት ሆኖ አላገኘውም” ብሏል፡፡

ይህን  የዋለልኝ ሃሳብ ብዙ አንባቢያንና ደራሲያን ይጋሩታል። ለመሆኑ ከመጽሐፍት ጀርባ በቅርብ ጓደኛ ወይም በታዋቂ ደራሲና ባለሙያ የሚጻፉ ምስክርነቶችን (ብለርብ) የይዘት ጥራት ደረጃ አመላካች አድርጎ መውሰድ ይቻላል? የብለርብ ዓላማና አስፈላጊነትስ ምንድን ነው? የሚለው እንደሚከተለው ተዘጋጅቷል፡፡

የመጽሐፍ የጀርባ አስተያየት (ብለርብ) ብዙ መጠሪያ አለው፡፡ የመጽሐፍ ጥቅል ሃሳብ፣ የመጽሐፍ ይዘት መግለጫ ወይም የመጽሐፍ ማስታወቂያ በሚሉት ሊገለጽ ይችላል፡፡ በእርግጥ ብለርብ በመጽሐፍ ላይ ብቻም ሳይሆን በፊልም እና በሌሎች ፈጠራዊ የጥበብ ስራዎችም ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል፡፡ በአጠቃላይ ስለመጽሐፉ የሚያስተዋውቅ፣ የመጽሐፍቱን ይዘት የሚገልጽ እንዲሁም ጸሐፊው ስለመጽሐፉ የተሰማውን ስሜት የሚገልጽበት ነው፡፡

ሃይለ ሚካኤል አበበ ጋዜጠኛ እና ደራሲ ነው፡፡ “የሥነ-አመራር ፍኖተ ጥበብ” የሚል የትርጉም፣ “አብርሆት” የተሰኘ ደግሞ የራሱን መጽሐፍ ለህትመት አብቅቷል፡፡ “ፍለጋ” በተሰኘው መጽሐፍ ላይ በአርትኦት ተሳትፏል፡፡ አሁን ደግሞ ሌላ መጽሐፍ ለማሳተም በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡

እንደ ሃይለ ሚካኤል ገለጻ፣ ከመጽሐፍት ጀርባ ላይ የሚጻፍ ጽሑፍ ዋና አላማው ስሜትን በሌሎች ላይ ማስተጋባትና ሰዎች እንዲያነብቡት በሚያስችል መልክ በጣም በአጭሩና በተመጠነ መንገድ መግለጽ ነው፡፡ “እኔ ሳነብበው ይህን መጽሐፍ እንደዚህ ተረድቸዋለሁ፤ እንዲህ አይነት ስሜት ሰጥቶኛል፣ እስኪ እናንተም አንብቡት” የሚል ግብዣ የሚቀርብበት ነው፡፡

በተጨማሪም ብለርብ ወደ ማስታወቂያ ያደላል፤ ሙያዊና ጥብቅ ሂሳዊ አስተያየት አይደለም፤ ሁለት፣ ሦስት ወይም ከዚያ በላይ ሰዎች ብለርብ ጽሑፍ ላይ ሊሳተፉ ይችላሉ፡፡ አጭር የግብዣ ማስታወቂያ ሊባልም ይችላል፡፡ ይህ ማለት ግን የተጋነነ ነገር ይጻፍበታል ማለት ሳይሆን ሚዛናዊ በሆነ መልኩና የመጽሐፉን ውስጣዊ ይዘት በሚገልጽ መልኩ መሆን እንዳለበት ደራሲ ሃይለ ሚካኤል ያብራራል፡፡

በተጨማሪም ብለርብ የተለመደው ከመጽሐፍ ጀርባ ነው፡፡ አንዳንዴም ግን የውስጥ ገጽ ላይ ሊጻፍ ይችላል፤ በውስጥ ገጽ የተለመደው በብዛት በውጭ ሀገራት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ግን አስተያየቱ የሚጻፈው በመጽሐፉ ጀርባ ላይ ነው፡፡

መጽሐፍ ሲገዛ ሦስት ምዕራፎች ያልፋሉ፡፡ ይህም ቅድመ ንባብ፣ የንባብ ወቅትና ከንባብ በኋላ ያለው ጊዜ ነው፡፡ ቅደመ ንባብ ላይ ከሚካተቱ ነገሮች ውስጥ አንዱ ብለርብ ነው፤ መጽሐፉን ያነበበው ሰው ምን ይላል፤ የጀርባ ጽሑፍ የጻፈው ሰው ማን ነው፤ ምን አስተያየት ሰጠ የሚለው ዋነኛው ነጥብ ነው፡፡

በእኛም ሀገር ሆነ በውጭ ደራሲዎች ብለርብ የሚያጽፉት በታዋቂ ደራሲያን ነው፡፡ በማህበረሰቡ ውስጥ ተጽእኖ መፍጠር የሚችሉ፣ ስምና ዝና ያላቸው ይጽፋሉ፡፡ በተቻለ መጠን የሚታመንና የሚወደድ ሰው ያደርጋሉ፡፡ ምክንያቱ የመጨረሻ ዓላማው ሌሎች ሰዎች አምነው እንዲገዙትና እንዲያነብቡት ነው፡፡

ይህም “እገሌ የተባለው ደራሲ ሐሳብ ከሰጠውማ ጥሩ ነው” በሚል አንባቢያን እንዲገዙት ለማድረግ ነው የሚለው ጋዜጠኛ እና ደራሲ ሃይለሚካኤል፣ ብለርብ ጸሐፊዎችን በሁለት መክፈል ይቻላል፡፡ አንዳንዶቹ ከቅርበት፣ ከጓደኝነትና አንዳንድ ጊዜም በክፍያ የተጋነኑ አስተያየቶችን ይጽፋሉ። አንዳንዶች ደግሞ በታማኝነትና በቅንነት “እኔ ይህን መጽሐፍ ሳነብ አንዳች ጥሩ ነገር አግኝቸበታለሁ፤ እናንተም ብታነቡት የሆነ ቁም ነገር ታገኙበታላችሁ፤ ደራሲውም ጀማሪ እንደመሆኑ መበረታታት አለበት” በሚል የሚያስቀምጡ ናቸው፡፡

ደራሲና ጋዜጠኛ ሃይለ ሚካኤል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባለው የወረቀትና ቀለም ዋጋ መናር፣ የህትመት ዋጋ መጨመር እና በመጽሔትና ጋዜጦች ላይ ይቀርብ የነበረው ሂስ መቀዛቀዝ ብለርብ የተጋነነና የመጽሐፉን ትክክለኛ የውስጥ ይዘት የማይገለጽ ሆኖ እንዲቀርብ አስተዋጽኦ አድርጓል ይላል፡፡

በዚህ ምክንያት የመጽሐፍን የጀርባ ጽሑፍ የሚጽፈው ሰው መጽሐፉን አጋንኖ፣ አድንቆ፣ ለየት ያለ የአጻጻፍ ጥበብ ይዞ የተከሰተ፣ በሀገራችን ሥነ ጽሑፍ አብሪ የሆነ፣ አዲስ የተወለደ ኮከብ ደራሲ ብለው  ይጽፋሉ ሲል ያብራራል፡፡ ይህ ደግሞ የሀገሪቱን ሥነ ጽሑፍ  እድገትና የንባብ ባህልን በከፍተኛ ሁኔታ ይጎዳል፡፡

ቅርብ ጊዜ ወዲህ በወዳጅነት ብቻ ብለርብ ይጻፋል፤ መጽሐፉን የማይገልጽ የተጋነነ  ሃሳብ ይሰጣል፤ ይህ ደግሞ በተለይ ጀማሪ ጸሐፍትን ሊያበረታታ አይችልም፤ እንዲያውም ሊጎዳቸው ይችላል፡፡

ደራሲና ጋዜጠኛ ሃይለሚካኤል አበበ፣ “ጓደኝነት ጠንከር ያለ ሂስ ለመስጠት ያስቸግራል፤ አንጋፋዎቹ ግን በፊት በፊት ወዳጅነት ቢኖራቸውም በድርሰት ጊዜ ጠንካራ ሃሳብ መለዋወጥ፣ ጋዜጣ ላይ ዱላ ቀረሽ ክርክር እስከ ማድረግ ይደርሱ ነበር፡፡ አሁን ግን ይህ ባህል እየቀረ መጥቷል፡፡ ጀማሪዎች በትክክለኛው መንገድ እንዲጓዙ የሚያደርግ አይደለም” በማለት ሁኔታውን ያስረዳል፡፡

“በእርግጥ አንደ ደራሲ ስራውን ሌሎች አንብበው አስተያየት ይስጡኝ ብሎ መውሰዱ በበጎ አይን የሚታይ ነው፡፡ ነገር ግን አስተያየቱ ትክክለኛ እና ሚዛናዊ አስተያየት መሰጠቱን ቢያረጋግጥ ጥቅሙ ለደራሲው ለራሱ ጭምር ነው፡፡ ምክንያቱም ለጊዜው ከሚሸጡ ጥቂት ኮፒ መጽሐፍት ይልቅ የዘመናት ታማኝነት የበለጠ ዋጋ አለው” የሚለው ሃይለ ሚካኤል፣ በእርግጥ ጀማሪ ጸሐፊዎች መጽሐፋቸውን አንብቦ አስተያየት የሚሰጣቸው ሰው ለመፈለግ የሚያደርጉት ጥረት ያለው አድካሚነት በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ አክሏል፡፡

ስለዚህ በቅንነትና በኃላፊነት ትልልቅ ደራሲዎች ጀማሪዎችን ማበረታታት እንዳለባቸው ያነሳል፡፡ ይሁን እንጂ በሀገሪቱ ባለው የኑሮ ውድነት ምክንያት አንዳንድ ብለርብ ጸሐፊዎች ትልልቅና ስም ያላቸው ደራሲዎች ጭምር  መጽሐፉን አንብበው አስተያየት እንዲጽፉ ሲጠየቁ ኑሮ ተወዷል፡፡ ጊዜዬን ነው የማጠፋው፣ አይኔን ነው የማቃጥለው፤ ስለዚህ የተወሰነ ክፍያ ያስፈልገኛል በሚል የሚጠይቁ  ሰዎች መኖራቸው የሚታወቅ ጉዳይ ነው፡፡

ችግር የሚሆነው ክፍያ መቀበላቸው ላይሆን ይችላል፡፡ ዋናው ችግር ገንዘብ ለተቀበሉበት ጉዳይ ምክንያታዊ ሆነው መጻፍ ላይ ክፍተቶች አሉ፡፡ ስለዚህ ይህ ከራስ ኃላፊነት፣ ቅንነትና ታማኝነት መነሳት አለበት፤ አንዳንድ ደራሲዎች ደግሞ አርአያ መሆን አለባቸው ሲል ሃይለ ሚካኤል ይመክራል፡፡

አክሎም የመጽሐፉን ይዘት በማይገልጽ መልኩ “አዲስ ምዕራፍ ተከፈተ፣ አዲስ ደራሲ ተወለደ” ብለው የሚጽፉ ሰዎች ለህሊናቸው ተገዥ ሆነው ሚዛናዊ አስተያየት መስጠት እንዳለባቸው ይታመናል፡፡ አንዳንድ ጸሐፊዎች ደግሞ ሙሉ መጽሐፉን ሳያነቡ አንብቡለት መልካም ጽሑፍ ነው ብለው የሚጽፉም አሉ፡፡

ሃይለሚካኤል፣ ታትሞ ሲወጣ እኔ የሰጠሁት አስተያየት ተቀየረብኝ የሚሉ፤ ደራሲው የሰጠውን አስተያየት ቀይሮ፣ ስሜን ተጠቅሞ የራሱን ሐሳብ ጻፈብኝ…” የሚል ቅሬታ ያላቸው ብለርብ ጸሐፊዎች መኖራቸውንም ያነሳል፡፡

አሁን አሁን ብለርብ ገበያ ተኮር እየሆነ መጥቷል፡፡ አሳታሚ ድርጅቶች ተከፋይ ብለርብ ጸሐፊ ቀጥረዋል፡፡ ዋና ዓላማቸው መጽሐፉ በብዛት እንዲሸጥ በማሰብ ነው ይላል ሃይለሚካኤል፡፡

ለዚህ መፍትሔ ብለርብ ተቋማዊ ቢሆን ይመረጣል፡፡ ተቋም ከሰው ይልቅ ኃላፊነት ይሰማዋል፡፡ የበለጠም ይታመናል፤ ግለሰብ ላይ አይንጠለጠለም፤ ሚዛናዊነት ይኖረዋል፡፡ ብለርብ ጸሐፊዎችና መጽሐፍ አሳታሚዎችም ለህሊናቸው ሊታመኑ ይገባል፡፡ አንድ አንባቢ አንድ ጊዜ እንደተሸጠ ከተሰማው በደራሲውም ሆነ በብለርብ ጸሐፊው ላይ ያለው እምነት ይጠፋል፡፡ ይህ ደግሞ ለደራሲያኑም ሆነ ለሀገራችን የድርሰት እድገት አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል ሲል በማጠቃለያ ሃሳቡ ላይ አንስቷል፡፡ በጋዜጣና መጽሄት ላይ ብለርብን ጨምሮ ሂስ ቢጠናከር ሲልም አክሏል፡፡

በመግቢያችን ላይ አስተያየት የሰጠን ዋለልኝ አየለ እንደሚለው ደግሞ ምንም እንኳን የጀርባ አስተያየት መጽሐፉን ለማስተዋወቅ ቢሆንም በመጽሐፉ ውስጥ ያለውን ድክመት መጥቀስም መለመድ እንዳለበት ያምናል፡፡ በውጭው ዓለም ይህ የተለመደ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ግን እንዲህ ቢደረግ ባለመጽሐፉ ደስተኛ ላይሆን ይችላል፡፡ ባለመጽሐፉ ደስተኛ አለመሆኑ ብቻም ሳይሆን አንባቢውም  መጽሐፉን አንብቤ የራሴን ፍርድ ልስጥ የማለት ባህሉ ምን ያህል ነው የሚለው አሳሳቢው ጉዳይ ነው ይላል፡፡

ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ (ዶ/ር) በዚሁ ጉዳይ ላይ ከሁለት ዓመት በፊት ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ በሰጠው አስተያየት ብለርብን እንደ መጽሐፉ ይዘት ለጉዳዩ ቅርብ የሆነ ሰው ቢጽፈው የተሻለ ነው ይላል፡፡ ይሄ ማለት ስለምጣኔ ሀብት የተጻፈ ከሆነ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ፣ ስለህክምና የተጻፈ ከሆነም የህክምና ሰው… ለልቦለድም ይሁን ለየትኛውም መጽሐፍ በዘርፉ ያለ ሰው አስተያየት ቢሰጥበት መጽሐፉን ለማስተዋወቅ ጭምር ጥሩ ይሆናል ይላል፡፡

የመጽሐፉን ህፀፅ መናገር የብለርብ ባህሪ አይደለም፤ ብለርብ፣ ሒስ እና ግምገማ ብዙ ጊዜ ይምታታል፤ ነገር ግን የተለያዩ ናቸው፡፡ ብለርብ ማለት አስተያየት ጻፍልኝ የተባለው ሰው ስለመጽሐፉ ያለው አስተያየት ነው። ይሄ ሲሆን የሚመረጠው ሰው ለመጽሐፉ ይዘት የቀረበ መሆን አለበት። ማንበብ ማንም ሊያነብ ይችላል፤ የመጽሐፍ ጀርባ አስታየት ሰጪው ግን መመረጥ አለበት፡፡ የመጽሐፉን ህፀፆች ለቅሞ በጀርባው መጻፍ ስህተት ነው፡፡ እዚያ ላይ የሚሰጠው ሒስ ሳይሆን መጽሐፉን በአጭሩ ማስተዋወቅ ነው፡፡ ህፀፆቹን ለማውጣት ከሆነ ሌላ የሒስ ጽሑፍ በጋዜጣ ወይም መጽሔት ወይም መድረክ ላይ መሥራት ነው ሲል ሃሳቡን አጋርቷል።

በአጠቃላይ የመጽሐፍ የጀርባ አስተያየት ሚዛናዊ፣ ትክክለኛ እና የመጽሐፉን ይዘት የሚገልጽ መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም ማጋነንና መጽሐፉን ከሚገባው በላይ መግለጽ የብለርብ ባህሪ አይደለም፡፡ በጓደኝነት ወይም መጽሐፉን ለማሻሻጥ ብቻ ተብሎ የሚሰጥ ከሆነ የማንንም ሳይሆን የአስተያየት ሰጪውን ክብር፣ ቀጥሎም የመጽሐፉን ደራሲ ክብርና ስም ዝቅ ያደርጋል፡፡

በጊዜው አማረ

 

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review