የጤና ተቋማት አቅም ምን ያህልእየጎለበተ ነው?

You are currently viewing የጤና ተቋማት አቅም ምን ያህልእየጎለበተ ነው?

ወልዶ መሳም፣ ዘርቶ መቃም፣ አስተምሮ ለቁም  ነገር ማድረስ… የሚባሉት የሰው ልጅ ፍላጎቶች እውን የሚሆኑት ጤና ሲኖር ነው፡፡ ጤናን ደግሞ አስቀድሞ መከላከል፣ የጤና እክል ሲያጋጥምም በቶሎ ወደ ህክምና ተቋማት መሄድ አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የጤና ተቋማትን አቅም ከነዋሪው ፍላጎት ጋር ማጣጣም ይገባል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዘርፉን አገልግሎት አሰጣጥ ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑ በ2017 በጀት ዓመት ከተገነቡት 28 የጤና ፕሮጀክቶች መካከል በሀምሌ ወር ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት የሆኑት 22 ጤና ጣቢያዎች ሁነኛ ማሳያዎች ናቸው።

ፕሮጀክቶችን የመረቁት የአዲስ አበባ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤም፣ “ጤና ጣቢያዎቹ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ከመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል አገልግሎት ጋር እኩል ደረጃ ያላቸው ሲሆን የሚሰጡት አገልግሎት ጥራት ከፍ እንዲል ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው በዘመናዊ የህክምና መሳሪያ ግብዓት እና ባለሙያዎች ጭምር እንዲደራጁ ተደርገዋል። እነዚህም ለከተማችን ነዋሪዎች ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጡ፤ ፍትሐዊ የጤና አገልግሎትን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ እንዲሁም በቅንነት፣ በትጋት እና በታማኝነት የማገልገል ማሳያችን ናቸው” ብለዋል።

የዝግጅት ክፍላችን ከፕሮጀክቶቹ አንዱ በሆነው በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ወረዳ 2 ጤና ጣቢያ ቅኝት አድርጓል፡፡ ወይዘሮ ሃስና ሙህዲን ያገኛቸውም በጤና ጣቢያው ህፃን ልጃቸውን ሲያሳክሙ ነው፡፡ ከዚህ በፊት እሳቸውም ሆኑ ቤተሰቦቻቸው ሲታመሙ ግራር ጤና ጣቢያ እና አለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ይታከሙ እንደነበር ገልፀው፤ ይህም ለእንግልት እና ለወጭ ዳርጓቸው መቆየቱን ያስታውሳሉ፡፡

“ከዚህ በፊት እታከምባቸው በነበሩ የጤና ተቋማት ወረፋ ይበዛ ነበር። በዚህም አንዳንድ ጊዜ ጠዋት 12፡00 ሰዓት ወጥቼ እስከ ቀኑ 10፡00 ሰዓት  ድረስ እንኳን ታክሜ አልመለስም ነበር” የሚሉት ወይዘሮዋ፤ አሁን ኮልፌ ወረዳ 2 ጤና ጣቢያ መሰራቱ ህክምናቸውን 1፡00 ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ወስጥ እንዲያጠናቅቁ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል፡፡

እንደ ወይዘሮ ሃስና ሁሉ ደስታቸውን በመግለፅ ሃሳባቸውን ሊያጋሩን የወደዱት ደግሞ በጤና ጣቢያው ህክምና ለያደርጉ መጥተው ያገኘናቸው አቶ ግርማ ተካ ናቸው፡፡ ተወልደው ያደጉት ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 ነው። የጤና አገልግሎት ለማግኘት ረጅም ርቀት ይጓዙ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታቸው ነው፡፡  ኮልፌ  ወረዳ 3 ጤና ጣቢያ፣ ዘውዲቱ መታሰቢያ   እና አለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሎች ለፊንጢጣ ኪንታሮት የቀዶ ህክምና አገልግሎት ሲያገኙ መቆየታቸውን  ነግረውናል፡፡

“በዚህ ቦታ የተገነባው ጤና ጣቢያ እንደ እኔ አቅመ ደካሞችና ርቀው ሄደው መታከም ለማይችሉ በቅርቡ እንዲታከሙ ያደርጋል፡፡ ከዚህ በፊት ሶስተኛም ሆነ አራተኛ ፎቅ ለመውጣት በእግራችን እንጓዝ  ነበር፡፡  አሁን ግን ሊፍት የተገጠመለትን እና ለእይታ የሚስብ ዘመናዊ ጤና ጣቢያ ተሰርቶልናል፡፡

ጤና ጣቢያው በቅርብ መሰራቱ ለትራንስፖርት የማወጣውን ወጪ፣ በወረፋና ትራንስፖርት በመጠበቅ የማባክነውን ጊዜ ቀንሶልኛል፡፡ ደረጃውን የጠበቀና ማራኪ መሆኑም አስደስቶኛል፤ የካራ ቆሪ ነዋሪዎች ይህን እድል በማግኘታችን እንኳን ደስ አላችሁ” ሲሉም ስሜታቸውን ገልፀዋል፡፡   

በጤና ጣቢያው አገልግሎት ሲሰጡ ካገኘናቸው የህክምና ባለሙያዎች ውስጥ የላቦራቶሪ ዲፓርትመንት ኃላፊው እያዩ አበበ አንዱ ናቸው፡፡ እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ ላቦራቶሪው የተሟላ፣ የተለያዩ የጉበት፣ ጥገኛ ትላትሎችና የመሳሰሉ በሽታዎች የሚታዩበትን ማሽኖች የያዘ ነው፡፡ 

በላቦራቶሪ ውስጥ ያለው “full automation” የሚባለው መመርመሪያ ማሽን በአንድ ጊዜ 40 ታካሚዎችን ማስተናገድ የሚችልና በነባር ጤና ጣቢያዎች የሌለ ነው፡፡ ስራውን ሙሉ በሙሉ ማሽኑ ስለሚሰራው የስራ ጫናን ከመቀነስ አንፃር አስተዋፅኦው የጎላ መሆኑንም ነግረውናል፡፡  

የጤና ጣቢያው ክፍሎች ሰፊ እና ጥራታቸውን የጠበቁ መሆናቸው ያለ ምንም መጨናነቅ ህክምና ለማድረግ የሚያግዝ እና የበሽታ መተላለፍን የሚቀንስ ነው፡፡ ህክምና ሊያደርግ የሚመጣው ማህበረሰብም ተገቢውን አገልግሎት አግኝቶ ደስተኛ ሆኖ ይመለሳል፡፡ 

በጤና ተቋሙ በሆስፒታል ደረጃ የሚሰራባቸው ማሽኖች መኖራቸው የአገልግሎት ተደራሽነቱ እንዲያድግ ያደርገዋል፡፡ ይህም ሆስፒታሎች ላይ የሚኖረውን የአገልግሎት ጫና ያቀልላል” ይላሉ፡፡ 

ሌላኛው በጤና ጣቢው የህክምና አገልግሎት ሲሰጡ ያገኘናቸው ጤና መኮንን አወቀ አንማው ናቸው፡፡ “ጤና ጣቢያውን ከዚህ በፊት ስሰራበት ከነበረው ኮልፌ ወረዳ 1 ጤና ጣቢያ ለየት የሚያደርገው በክፍሎቹ አሰራርና ስፋት እንዲሁም ደረጃቸውን የጠበቁ የህክምና መሳሪያዎች የተሟሉለት ሆኖ መሰራቱ ነው” ብለዋል፡፡ 

ጥራታቸውን ጠብቀው የተሰሩ ጤና ጣቢያዎች የህክምና ባለሙያው ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጥ፣ የሚገለገለው የማህበረሰብ ክፍልም ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኝ ከማድረግ በተጨማሪ በሆስፒታል ደረጃ ያለውን ወረፋ እንዲሁም የስራ ጫና የሚቀንስ በመሆኑ አስተዋፅዋቸው የጎላ እንደሆነ ጤና መኮንኑ ነግረውናል፡፡  

የጤና ጣቢያው ስራ አስኪያጅ አቶ አሳዬ ገዳሙ በበኩላቸው፤ በወረዳው የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች ህክምና ሲያገኙ የቆዩት ረጅም ርቀት በመሄድና የትራንስፖርት በማውጣት በአጎራባች ወረዳዎች ነበር፡፡ ይህ ያማረረው ነዋሪም በወረዳው ጤና ጣቢያ እንዲሰራለት ለረጅም ጊዜ ሲጠይቅ ቆይቷል፡፡ በዚህም መሰረት አዲስ ጤና ጣቢያ እንዲገነባ ሆኗል ይላሉ፡፡  

በወረዳው ጤና ጣቢያ ባለመኖሩ ከዚህ በፊት ነዋሪው ህፃናትን ተከታትሎ ለማስከተብ ሲቸገር፣ በዚህም ለወረርሽኝ ሲዳረግ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ሁሉንም አገልግሎት በቅርብ የሚያገኝበት እድል ተፈጥሯል፡፡

ጤና ጣቢያው የድንገተኛ አገልግሎት፣ የመድኃኒት፣ የላቦራቶሪ፣ የማዋለድ፣ የአዋቂዎችና የህፃናት የተመላላሽ ህክምና፣ የክትባት እና የነፍሰ ጡር እናቶች ክትትል አገልግሎቶችን እንዲሰጥ ታስቦ የተሰራ ነው፡፡

እንደ ስራ አስኪያጁ ገለጻ፣ ጤና ጣቢያው 15 አልጋዎች አሉት፤ 48 ሺህ ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችም አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ ይታሰባል። ከሌሎች ወይም በፊት ከተሰሩት ጤና ጣቢያዎቸ ለየት የሚያደርገው ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስፈልጉ የቀዶ ህክምና ክፍሎችና መሳሪዎች አሉት፤ አካል ጉዳተኞችና አቅመ ደካሞች እንደልባቸው የሚንቀሳቀሱበት አሳንሰር ወይም ሊፍት ተገጥሞለታል፡፡ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ትስስር ለመፍጠር የሚያስችሉ ገመዶች በውስጥ ተሰርተውለታል፡፡     

ህብረተሰቡ ህመሙ ሳይብስ በአካባቢው ጥራት ያለው ህክምና ማግኘት መቻሉ ሆስፒታል ሄዶ የሚፈጥረውን ጫና ይቀንሳል፡፡ የአስተኝቶ ህክምና እና ዘመናዊ ማሽኖች የተገጠሙለት በመሆኑ በሆስፒታሎች ላይ የሚታየውን የሃኪሞች የስራ መደራረብ በመቀነስ ረገድ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ማህበረሰቡንም ከአላስፈላጊ ወጪ እና እንግልት የሚታደግ ነው ሲሉ የሆስፒታሎችን የአገልግሎት አሰጣጥ ጫና የሚቀንስ መሆኑን ነግረውናል፡፡

ጤና ጣቢያው ከአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጋር ትስስር ፈጥሮ በመስራት የማህበረሰቡን ፍላጎት ለማሟላት እየተጋ እንደሚገኝ የገለፁት ስራ አስኪያጁ፤ ከሆስፒታሉ የህክምና ባለሙያዎች ጋር በመሆንም በቅርቡ የቀዶ ህክምና አገልግሎታቸውን እንደሚጀምሩ አብራርተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ የፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለማየሁ ወንድሙም፣ አዳዲስ የተገነቡና ማስፋፊያ የተደረገላቸው ጤና ጣቢያዎች በሆስፒታሎች አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያለውን ጫና በመቀነስ ረገድ ጉልህ ድርሻ አላቸው፡፡ እናቶች በሆስፒታሎች በቀዶ ህክምና ይወልዱ የነበረውን በጤና ጣቢያዎቹ እንዲወልዱ የሚያስችል መሆኑ፣ የጥርስ፣ የዓይንና ቆዳ ህክምናዎች መስጠት የሚችሉ መሆናቸው በማሳያነት የሚጠቀስ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ 

አዳዲስ ከተገነቡት ውስጥ አምስቱ ምንም ጤና ጣቢያ በሌለባቸው ቦታዎች የተሰሩ እና አራቱ ደግሞ ከደረጃ በታች የነበሩ ጤና ጣቢያዎችን በማፍረስ የተሰሩ ናቸው፡፡ እነዚህ የተመረቁት ጤና ጣቢያዎች ከዚህ በፊት አገልግሎት ይሰጡ ከነበሩት ነባር ጤና ጣቢያዎች የሚለዩት በፊት ከሚሰጡ በተጨማሪ ሌሎች አገልግሎቶችን እንዲሰጡ ታሳቢ ተደርጎ የተገነቡና ማስፋፊያ የተደረገላቸው ናቸው፡፡ በዋናነትም የተገነባባቸው ቁሳቁስ ጥራት፣ ተላላፊ የሆኑ እንደ ቲቢ ያሉ በሽታዎች ከህመምተኛው ወደ ጤነኛው በቀላሉ እንዳይተላለፉ ታሳቢ ተደርጎ መሰራታቸው፣ ዲዛይናቸው፣ ከዚህ በፊት ያልተለመደ ቀዶ ህክምና አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጋቸው፣ እያንዳንዱ ክፍሎች ሰፋፊ እና ደረጃቸውን የጠበቁ እና አሳንሰር የተገጠመላቸው መሆናቸው በአጠቃላይ አገልግሎት መስጫ ክፍሎቹ ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ መሰራታቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንደ ከተማ ከጤና አንፃር የተደራሽነት ችግር እንደሌለ የነገሩን የፅህፈት ቤት ኃላፊው፤ እነዚህ ጤና ጣቢያዎች ፍትሐዊ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡና በሰው ሃይልና በግብዓት ተደራጅተው ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ መሆናቸውንም አክለዋል፡፡

በፋንታነሽ ተፈራ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review